ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ኢትዮጵያ መድን ከ አዳማ ከተማ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ኢትዮጵያ መድን ከ አዳማ ከተማ

በሁለት የተለያዩ ፅንፎች ባሉ ፎክክሮች ውስጥ የሚገኙ ክለቦችን የሚያፋልመው ጨዋታ ለቡድኖች ካለው አስፈላጊነት አንፃር ብርቱ ፍልሚያ ይደረግበታል ተብሎ ይገመታል።

በሰንጠረዡ አናት እና ግርጌ የሚገኙት ቡድኖችን የሚያገናኛው ጨዋታ ውጤት ለሁለቱም የተለያየ ትርጉም ይኖረዋል። ለመድን ከተከታዩ ጋር ያለውን ልዩነት ይበልጥ አስፍቶ በዋንጫ ፉክክሩ አንድ እርምጃ ለመራመድ  የሚያደርገው ጥረት ውስጥ የሚከወን ጨዋታ ነው። በተቃራኒው አዳማ ከተማ ቢያንስ ከበላዩ ያለው ሀዋሳ ከተማ ጋር በነጥብ ለመስተካከል እና ላለመውረድ በሚደርገው ፍልሚያ ውስጥ ተስፋን የሚያልምበት ጨዋታ ይሆናል።

የነገው ጨዋታ በኢትዮጵያ መድን የዋንጫ ጉዞ ላይ
ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ወሳኝ መርሐግብር ነው። በመጨረሻው ጨዋታ ከሦስት ተከታታይ ድሎች በኋላ ነጥብ መጣሉን ተከትሎ በዋንጫ ፉክክሩ አንድ እርምጃ ለመራመድ ከነገው ፍልሚያ ሙሉ ነጥብ ማሳካት ግድ የሚለው መሪው መድን ከተከታዮቹ ሁለቱም ማለትም ባህር ዳር ከተማ እና ወላይታ ድቻ ነጥብ መጣላቸውን ተከትሎ ዳግም የነጥብ ልዩነቱን የሚያሰፋበት ወርቃማ ዕድል እጁ ውስጥ ገብቷል። በነገው ጨዋታ ድል ማድረግ ከቻለም በዛሬው ዕለት ድል ካደረገውና በ2ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው ኢትዮጵያ ቡና ያለው የነጥብ ልዩነት ወደ ዘጠኝ የሚያሰፋበት ዕድል በዚህ ጨዋታ ውስጥ ይገኛል።

በመጨረሻው ሳምንት ሳይጠበቅ በግርጌው በተቀመጠው ወልዋሎ ነጥብ የጣለው መድን የተከላካይ ክፍሉ ወሳኝ ተሰላፊዎች በጉዳት ማጣቱ ፈተናው ሆኖ ቆይቷል፤ በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ለግብ ማስተናገድ የተገደደው ቡድኑ ዋነኛ ጠንካራ ጎኑ ሆኖ የዘለቀው የመከላከል ብርታቱ መመለስ ይኖርበታል፤ በመጨረሻው ጨዋታ ከጉዳት የተመለሰው ረመዳን የሱፍ  ማግኘታቸውም ለአሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ጥሩ ዜና ነው። በነገው ዕለትም ባለፉት አራት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ያስቆጠረው አዳማ ከተማ እንደመግጠሙ ከባድ ፈተና ይጠብቀዋል ተብሎ ባይገመትም ጨዋታው ለተጋጣሚው ካለው ወሳኝነት አንፃር ግን ምናልባትም እንደባለፈው ሳምንት ዓይነት ያልተጠበቀ ፍልሚያ ሊጠብቀው የሚችልበት ዕድልም አለ።

በሃያ አንድ ነጥቦች 16ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አዳማ ከተማዎች ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት በሚያደርጉት ጉዞ አስፈላጊ ነጥብ ለመሸመት መሪውን ይገጥማሉ።

15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ሀዋሳ ከተማ በትናንትናው ጨዋታ ድል ማድረጉን ተከትሎ ልዩነቱን ለማጥበብ እያለሙ ወደ ሜዳ የሚገቡት አዳማ ከተማዎች የነገውን ጨምሮ ቀጣይ ጨዋታዎች ላይ የሚያገኟቸው ነጥቦች ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት በሚያደርጉት ጉዞ እጅግ ወሳኝ ናቸው። አዳማዎች በነገው ዕለት  ድል ቢቀናቸውም የደረጃ መሻሻልን የሚያገኙበት ዕድል ጠባብ ቢሆንም ከቅርብ ተፎካካሪዎቻቸው ላለመራቅ ግን ጨዋታውም በድል መወጣት አስፈላጊያቸው ነው። ባለፉት አራት ጨዋታዎች ድል ያላደረጉት እና በመርሐ-ግብሮቹ ማግኘት ከሚገባቸው አስራ ሁለት ነጥቦች አስሩን በመጣል ሁለቱን ብቻ ያሳኩት አዳማዎች ከነገው ጨዋታ ነጥብ ይዞ ለመውጣት በሁሉም ረገድ መሻሻል ይኖርባቸዋል፤ በተለይም በተጠቀሱት ጨዋታዎች ስድስት ግቦች ያስተናገደው እና የወጥነት ችግር የሚታይበት የቡድኑ የኋላ ክፍል ከተጋጣሚው ጥንካሬ አንፃር የሚጠብቀው ፍልሚያ ከባድ ስለሆነ በሁሉም ረገድ ተሻሽሎ መቅረብ አለበት።

በኢትዮጵያ መድን በኩል በረዥም ጊዜ ጉዳት ላይ ያለው ሚሊዮን ሰለሞን አሁንም ከነገው ጨዋታ ውጭ ነው። በአዳማ ከተማ በኩል ግን ሁሉም የቡድን አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በሊጉ 23 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን አዳማ 7 ጨዋታ በማሸነፍ ቀዳሚ ነው። መድን 5 ሲያሸንፍ 11 ጨዋታ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ነበሩ ፤ አዳማ 26 ሲያስቆጥር መድንም በተመሳሳይ 26 አስቆጥሯል።