ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድኖች መሪነታቸውን አጠናክረዋል

ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድኖች መሪነታቸውን አጠናክረዋል

በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን አዳማ ከተማን 3ለ1 በማሸነፍ 14ኛ የውድድር ዘመን ድሉን ሲያሳካ ሊጉንም በዘጠኝ ነጥቦች ልዩነት መምራት ጀምሯል።

የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን ከወልዋሎ ጋር  ነጥብ ከተጋራበት ስብስብ የሁለት ተጫዋች ለውጥ ሲያደርጉ በዚህም ዋንጫ ቱት እና ዳዊት አውላቸውን በታዬ ጋሻው እና በመሀመድ አበራ ተክተው ወደ ሜዳ ሲገቡ አዳማ ከተማ በበኩሉ ከወላይታ ድቻ ጋር ያለ ጎል በተጠናቀቀው ጨዋታ ከተጠቀመበት ስብስብ መላኩ ኤልያስን አሳርፈው ኃይለሚካኤል አደፍርስን ለውጠው አስገብተዋል።

የሊጉን ሦስተኛ ጨዋታውን በመራው በዋና ዳኛ ፍቅሩ ለገሰ ባስጀመሩት ጨዋታ በሁለቱም በኩል በስታዲየሙ እየጣለ የነበረው ከባድ ዝናብ ሳይበግራቸው ቶሎ ቶሎ ወደ ማጥቃት ክልል ውስጥ ለመግባት በሚደረግ ምልልሶች የጨዋታው ጥራት ከፍ ብሎ እንዲጀምር አድርጎታል።

በተለይ የመሐል ሜዳውን የበላይነት ለመውሰድ የነበረው ፉክክር የጨዋታውን ቀሪ ደቂቃዎች በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎታል ፤ በዚህም 21ኛው ደቂቃ ኢትዮጵያ መድኖች በአስደናቂ የማጥቃት ሽግግር ጥራት ያለው ጎል አስቆጥረዋል። መነሻውን ከመሐል ዳዊት ተፈራ ያደረገው ኳስ በግራ መስመር ከጀርባ ለመጣው ያሬድ ካሳይ ደርሶት በጥሩ ሁኔታ ያሻገረውን አጥቂው መሐመድ አበራ ዘሎ በግንባሩ በመግጨት ኳስ እና መረብን አገናኝቷል።

አዳማ ከተማዎች ጎል ከተስተናገደባቸው በኋላ ወደ ጨዋታው ለመመለስ መንቀሳቀስ ቢችሉም በጥንቃቄ እና ብስለት በተሞላበት መንገድ ኳሱን በመቆጣጠር ወደ ፊት የሚሄዱት መድኖች ሁለተኛ ጎላቸውን 35ኛው ደቂቃ ላይ አግኝተዋል።

ከሳጥን ውጭ ወደ ግራ ባደላ ቦታ አቡበከር ኑራ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን ቅጣት ምት ባለብዙ ልምዱ ሀይደር ሸረፋ ወደ ግብነት ቀይሮታል።

45ኛው ደቂቃ ላይ የሁለት ተጫዋቾች ፈጣን ቅያሪ ያደረጉት አዳማዎች በተለይ በማጥቃቱ በኩል ለቡድኑ አቅም እንዲጨምር ታስቦ የገባው አጥቂው ስንታየሁ መንግስቱ ከሙሴ ከበላ የተላከለትን ኳስ አሸንፎ በመግባት በግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ እግር ስር አሾሉኮ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታ ከዕረፍት መልስ እንዲጠበቅ አድርጎት ወጥቷል።

በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 51ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ተፈራ ከማዕዘን ምት ያሻገረውን ለመጀመርያው ጎል መቆጠር ትልቁን ድርሻ የሚወስደው ያሬድ ካሳዬ በግንባሩ በመግጨት የመድኖችን የጎል መጠን ወደ ሦስት ከፍ አድርጎታል።

ከአንድ ደቂቃ በኋላ መድኖች ከቅጣት ምት የተነሳውን አለን ካይዋ በግንባሩ የገጨዋን ግብጠባቂው ናትናኤል እንደምንም አድኖበታል።

ሦስት ጎል ተቆጥሮባቸው የበላይነት የተወሰደባቸው አዳማዎች ከመውረድ ይልቅ በቅንቅስቃሴ ውስጥ በመቆየት ጎል ለማስቆጠር ጥረት ማድረጋቸውን ቀጥለው በተለይ 58ኛው ደቂቃ ስንታየሁ መንግስቱ ተከላካይ በመቀነስ በጠንካራ ምት ወደ ጎል የላከውን ኳስ የግቡ አግዳሚ ጎል እንዳይሆን ከልክሎታል።

ሦስት ጎል በማስቆጠራቸው ያልቆሙት ኢትዮጵያ መድኖች ጨዋታውን ክፍት አድርገው ተጨማሪ ጎል ለማግኘት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጨዋታውን ማራኪ ፉክክር እያስመለከተን እንዲቀጥል አድርጎታል። በዚህም 68ኛው ደቂቃ ወገኔ ገዛኸኝ ከርቀት በጠንካራ ምት ወደ ጎል የሞከረውን በግብ ጠባቂው ናትናኤል መክኖበታል።

በመጨረሻዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች ኳሱን ተቆጣጥረው መጫወታቸውን የቀጠሉት ኢትዮጵያ መድኖች ለቀጣይ ጨዋታ በማሰብ የቡድኑን ቁልፍ ተጫዋቾች በመቀየር እና በረመዳን የሱፍ እና በመሐመድ አበራ አማካኝነት ከፈጠሩት የጎል ዕድሎች ውጭ ተጠቃሽ ሙከራዎች ሳይደረግ ጨዋታውን 3-1 በማሸነፍ ወደ ዋንጫው የሚያደርጉትን ጉዞ አጠናክረው ቀጥለዋል።