ከነገ ዓርብ እስከ ሰኞ እንደሚደረጉ ይጠበቁ የነበሩት የ26ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ላይ ማስተካከያ መደረጉ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሀዋሳ ከተማ ሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም እየተደረገ እንደሚገኝ ይታወቃል። የሊጉ መርሐ-ግብር እንደ አዲስ በተሰራው የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ ከሰሞኑን በከተማው በጣለው ከባድ ዝናብ ሜዳው ማጫወት አለመቻሉና የ25ኛ ሳምንት የመዝጊ መርሐ-ግብር የነበረው የድሬዳዋ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታ ለሌላ ጊዜ መራዘሙ ይታወቃል።
የጣለው ዝናብ ከባድ በመሆኑና ነገ የሚጀምረውን የ26ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ለማድረግ ሜዳው ዝግጁ ስላይደለ ማስተካከያ ማድረግ አስፈልጎ መርሐ-ግብሮቹ ላይ የቀናት መሸጋሸግ መደረጉን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል። በዚህም ዓርብ ሊደረጉ የነበሩ ጨዋታዎች ቅዳሜ፣ ቅዳሜ ሊደረጉ የነበሩ ጨዋታዎች እሁድ፣ እሁድ ሊደረጉ የነበሩ ጨዋታዎች ሰኞ እንዲሁም ሰኞ ሊደረጉ የነበሩ ጨዋታዎች ማክሰኞ እንዲደረጉ ውሳኔ ላይ መደረሱ ታውቋል።
ከዚሁ መርሐ-ግብር ጋር በተገናኘ እሁድ ጠዋት 3:30 እንዲደረግ ቀጠሮ ተይዞላቸው የነበሩት አዳማ ከተማ እና መቻል ሜዳው የዛን ቀን ማጫወት ከቻለ ቀድሞ በተያዘው መርሐ-ግብር መሰረት ጨዋታውን እንዲያደርጉ ጥያቄ ማቅረባቸውን ሰምተናል።