ሊጠናቀቅ የሁለት ሣምንታት ጨዋታዎች በቀሩት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ “ለ” ሁለት ቡድኖች ለአሸናፊነት ተፋጠዋል።
በኢዮብ ሰንደቁ
በ2018 ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሚያድጉትን ቡድኖች ለመለየት የሚደረገው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ወደ መጠናቀቁ ተቃርቧል። ምድበ “ሀ” አስቀድሞ ሻምፒዮኑን እና ቀጣይ ወደ ፕሪምየር ሊግ ያደገውን ቲም እንዲሁም ወደ ሊግ አንድ የወረዱ አራቱን ቡድኖች በጊዜ ያሳወቀ ሲሆን ሸገር ከተማም በ48 ነጥብ ውድድሩን አንደኛ ሁኖ በመጨረስ ቀጣይ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከምንመለከታቸው አዲስ አዳጊ ቡድኖች አንዱ መሆን ችሏል።
ይሁን እንጂ ሊጠናቀቅ ሁለት ጨዋታዎች በቀሩት ምድብ “ለ” ሁለት ክለቦች ለአሸናፊነት ተፋጠዋል። እነሱም በሁለት ነጥብ ልዩነት 1ኛ እና 2ኛ ላይ የተቀመጡት ነገሌ አርሲ እና ደሴ ከተማ ናቸው።
ለረጅም ሳምንታት እየተፈራረቁ መሪነታቸውን ካቆዩት ክለቦች ውድድሩ በማን አሸናፊነትን ይጠናቀቃል የሚለው ጥያቄ የብዙኃኑን ቀልብ ስቧል። በ21ኛ ሳምንት መርሐግብር ነገ ሁለቱም ክለቦች ነገሌ አርሲ ከ ስልጤ ወራቤ እንዲሁም ደሴ ከተማ ከ የካ ክ/ከተማ ጋር በተመሳሳይ ሰዓት 5:00 ሲል ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ለማደግም ሆነ ወደ ሊግ አንድ ላለመውረድ በሚደረገው ትንቅንቅ የምድቡ መሪ የሆኑት ነገሌ አርሲዎች የነገውን ጨዋታ አሸንፈው ደሴዎች ነጥብ ሚጥሉ ከሆነ ከ ሸገር ከተማ በመቀጠል ወደ ፕሪሚየር ሊግ የሚያስገባቸውን ትኬት የቆረጡ ሁለተኛው ቡድን ይሆናሉ።