በሳምንቱ የመጀመሪያ መርሐግብር ሀዲያ ሆሳዕና ወላይታ ድቻን 3ለ1 አሸንፏል።
09፡00 ሲል በዋና ዳኛ ባሕሩ ተካ መሪነት የተጀመረው ጨዋታ ማራኪ የሆነ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ በማስመልከት ነበር አሃዱ ያለው። የጦና ንቦቹ ገና በ5ኛው ደቂቃ ጨዋታውን ሊመሩ እጅግ ተቃርበው ያሬድ ዳርዛ ከካርሎስ ዳምጠው በተቀበለው ኳስ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገውን ሙከራ የግቡ የቀኝ ቋሚ መልሶበታል።
ጎል ከማስተናገድ የተረፉት ነብሮቹ 7ኛ ደቂቃ ላይ ግብ የሚያስቆጥሩበትን ወርቃማ ዕድል አግኝተው ተመስገን ብርሃኑ ከመሃል በተሰነጠቀለት ኳስ ግብ ጠባቂውን በማለፍ ያደረገውን ሙከራ ተከላካዩ ኬኔዲ ከበደ መልሶበታል። ይህም እጅግ አስቆጪው የሀዲያዎች አጋጣሚ ነበር።
በሳቢነቱ የቀጠለው ጨዋታ 30ኛ ደቂቃ ላይ ጎል ተቆጥሮበታል። በየነ ባንጃ ያቀበለውን ኳስ ናትናኤል ሞገስ ወደ ግብ መትቶት ግብ ጠባቂው አብነት ሀብቴ በእግሩ የመለሰውን ኳስ ያገኘው ብሩክ በየነ ጎል አስቆጥሮ ነብሮቹን መሪ አድርጓል።
የነብሮቹ መሪነት ግን ከሁለት ደቂቃዎች ማለፍ አልቻለም ያሬድ ዳርዛ ከሳጥን ውጪ በግሩም ሁኔታ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ያሬድ በቀለ ሲመልሰው ያገኘው ዘላለም አባተ ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፎ የጦና ንቦቹን ወደ አቻነት መልሷል። ይህም የአጋማሹ የመጨረሻ የግብ ዕድል ሆኖ ጨዋታው ወደ ዕረፍት አምርቷል።
ከዕረፍት መልስ የጨዋታው ግለት በመጠኑ ሲቀንስ በሴኮንዶች ልዩነት ተመስገን ብርሃኑ ከሳጥን ውጪ ባደረገው እና ግብ ጠባቂው በያዘበት ኳስ ሙከራ ማድረግ የቻሉት ነብሮቹ 58ኛው ደቂቃ ላይም ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው ብሩክ በየነ ያመቻቸለትን ኳስ ተመስገን ብርሃኑ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ሞክሮት በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።
እየተቀዛቀዙ የሄዱት ወላይታ ድቻዎች 63ኛው ደቂቃ ላይ አብነት ደምሴ ከረጅም ርቀት መትቶት በሌላ ተጫዋቾች ከተጨረፈ በኋላ ያገኘው ካርሎስ ዳምጠው ሞክሮት በግቡ አግዳሚ ከወጣበት ሙከራ ውጪ ይህ ነው የሚባል የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል።
ቀስ በቀስ ብልጫውን እየወሰዱ የሄዱት ሀዲያ ሆሳዕናዎች 71ኛ ደቂቃ ላይ መሪ መሆን ችለዋል። በየነ ባንጃ ራሱ ከመሃል ያስጀመረውን ኳስ ተመስገን ብርሃኑ መልሶ ሲያቀብለው የድቻው ተከላካይ መልካሙ ቦጋለ ኳሱን ለማራቅ ሲሞክር ተደርቦ በመመለስ እና ራሱን ተከላካዩን አታልሎ በማለፍ ድንቅ ጎል ከመረብ ማሳረፍ ችሏል።
ጨዋታውን መምራት ከጀመሩ በኋላ በራስ መተማመናቸውን የጨመሩት ነብሮቹ 80ኛ ደቂቃ ላይ ሦስተኛ ጎል አስቆጥረዋል። በየነ ባንጃ ከካርሎስ ዳምጠው ታግሎ የነጠቀውን ኳስ ተቀይሮ ለገባው ደስታ ዋሚሾ አቀብሎት ደስታም በሳጥኑ የግራ ክፍል ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ በጥሩ አጨራረስ አስቆጥሯል። ጨዋታውም በሀዲያ ሆሳዕና 3ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።