ቅዱስ ጊዮርጊስ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲን 3-1 በማሸነፍ ከስምንት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል የተመለሰበትን ውጤት አስመዝግቧል።
በኢዮብ ሰንደቁ
በ27ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በምሽቱ ጨዋታ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩንቨርስቲን ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ አገናኝቷል። ባሳለፍነው ሳምንት ከስሑል ሽረ ጋር ነጥብ የተጋሩት ወልዋሎዎች ይዘውት ከገቡት አሰላለፍ ግብጠባቂውን ኦሎሩንለኬ ኦሉዋሴንጎ፣ ኪሩቤል ወንድሙ፣ ናሆም ሃይለማርያም፣ የዓብስራ ሙሉጌታ እና ዳዊት ገብሩን በማስወጣት በእነርሱ ምትክ በረከት አማረ፣ ሳሙኤል ዩሃንስ፣ ሙሳ ራመንታ፣ ስምዖን ማሩ እና ፋዓድ አዚዝን ሲያስገቡ በተመሳሳይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በኢትዮጵያ በንግድ ባንክ ነጥብ ከጣሉበት አሰላለፍ ግብጠባቂው ተመስገን ዩሃንስ፣ ሀብታሙ ጉልላት፣ ብሩክ ታረቀኝ፣ አብርሃም ጌታቸው፣ ፍፁም ጥላሁንን በማሳረፍ በምትካቸው ባህሩ ነጋሽ፣ አሸናፊ ጌታቸው፣ ጳውሎስ ከንቲባ፣ ፉዓድ አብደላ እና ቢንያም ፍቅሩን በማስገባት ጨዋታቸውን ጀምረዋል።
ጨዋታው ገና በመጀመሪያው ደቂቃ ጎል ያስመለከትን ጨዋታ ነበር። በ1ኛው ደቂቃ በረከት ወልዴ ከመሐሉ የሜዳ ክፍል ያቀበለውን ኳስ ቢንያም ፍቅሬ የተከላካዮችን መዘናጋት ተጠቅሞ ቅዱስ ጊዮርጊስን ገና ከጅማሬው መሪ ማድረግ ችሏል።
ከግቡ መቆጠር በኋላ ወልዋሎ ዓዲግራቶችም ባልተጠበቀ ሰዓት እና ሁኔታ የገባባቸውን ጎል ለማካካስ በኳስ ቁጥጥር እና በጨዋታ እንቅስቃሴ ብልጫ በመውሰድ ጫና በመፍጠር ሲጫወቱ በተቃራኒው ቅዱስ ጊዮርጊሶች ጥንቃቄ የተሞላበትን ጨዋታ ምርጫቸው አድርገዋል። ወልዋሎዎች ጫና ፈጥረው መጫወት ቢችሉም ኳስን ከመረብ ማሳረፍ ሳይችሉ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ወልዋሎዎች ድካማቸው ፍሬ አፍርቶ አቻ የሆኑበትን ግብ ማስመዝገብ ችለዋል። 68ኛው ደቂቃ ላይ ሙሳ ራመታን ያቀበለውን ኳስ ቡልቻ ሹራ ጥሩ በሆነ አጨራረስ የቀድሞ ክለቡ ላይ ግብ በማስቆጠር ወልዋሎዎችን አቻ ማድረግ ችሏል።
የአቻነት ግቡ መቆጠር ቁጭት የፈጠረባቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች ጨዋታውን በመቀየር በእንቅስቃሴ ረገድ ብልጫ ወስደዋል ጨዋታቸውንም ረጅም ኳስ በመጠቀም ለማጥቃት ሙከራ ሲያደርጉ ተስተውሏል። 69ኛው ደቂቃ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከረጅም ርቀት ያሻገሩትን ኳስ አማኑኤል ኤርቦ ግብ ቢያስቆጥርም በአወዛጋቢ ሁኔታ የዕለቱ ዳኛ ግቡን ሽረውታል።
ይበልጥ ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት ፈረሰኞች ግብ ማስቆጠር ችለዋል። 81ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻማውና ቢኒያም ፍቅሩ የገጨው ኳስ የደረሰው ተቀይሮ የገባው አብዱ ሳሚዮ ግብ በማስቆጠር ዳግም ፈረሰኞችን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከግቡ ከተቆጠረ ከሰባት ደቂቃ በኋላ የወልዋሎዎችን ተስፋ የሰበረ ግብ ቅዱስ ጊዮርጊሶች አስቆጥረዋል። 88ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ዳግማዊ አርአያ በጥሩ ሁኔታ አታሎ ወደ ሳጥን በመግባት ያቀበለውን ኳስ ቢንያም ፍቅሩ ወደ ግብነት በመቀየር ለራሱ ሁለተኛውን ለክለቡ ደግሞ ሶስተኛ ግቡን ማስቆጠር ችሏል። ጨዋታውም በቅዱስ ጊዮርጊስ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።