ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ባስቆጠራቸው ግቦች ሲዳማ ቡና ሦስተኛውን ተከታታይ የ1ለ0 ድል ኢትዮጵያ ቡናን በማሸነፍ ተቀዳጅቷል።
በኢዮብ ሰንደቁ
በ26ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን 9 ሰዓት ላይ ኢትዮጵያ ቡናን ከ ሲዳማ ቡና ሲያገናኝ ኢትዮጵያ ቡናዎች ፋሲል ከነማን ድል ካደረጉበት አሰላለፍ ረጅብ ሚፍታህን በእያሱ ታምሩ በመቀየር ሲጀምሩ በተቃራኒው ሲዳማ ቡናዎች ባህር ዳርን ካሸነፉበት አሰላለፍ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ጨዋታቸውን ጀምረዋል።
ጨዋታው ሁለት ከአሸናፊነት የተመለሱ ክለቦች መካከል የተደረገ ውድድር እንደመሆኑ መጠን አጓጊ እና ሳቢ ጨዋታ ሊኖር እንደሚችል በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ የተገመተ ጨዋታ ነበር። ጨዋታው ጅማሬዎቹ ላይ በሁለቱም ክለቦች በኩል ጥሩ እንቅስቃሴን ያሳየን ሲሆን ሲዳማ ቡናዎች ግብ ማስቆጠር ችለዋል። 13ኛው ደቂቃ ላይ መነሻውን ከቀኝ መስመር ያደረገ ኳስ ማይክል ኪፕሩቪ በጥሩ ሁኔታ አታልሎ ወደ ሳጥን በመግባት ያቀበለውን ኳስ ጥሩ ሁኔታ ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን ወደ ግብነት በመቀየር ሲዳማዎችን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከግቡ መቆጠር በኋላ ኢትዮጵያ ቡናዎች የአቻነት ግብ ፍለጋ በቁጥር እና በኳስ ብልጫ በዛ ብለው ኳስን ከራሳቸው የግብ ክልል መስርቶ አንድ ሁለት በሆነ ቅብብል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉ ሲሆን በአንተነህ ተፈራ አማካኝነት ሁለት ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉ ሲሆን ግብ ማስቆጠር ግን ሳይችሉ ቀርተዋል። በተቃራኒው ሲዳማዎች ወደ ኋላ በማፈግፈግ ጥንቃቄን ምርጫ በማድረግ በመልሶ ማጥቃት ከርቀት በሚጣሉ ረጅም ኳሶች ግብ ለማግኘት ሲጫወቱ ተስተውሏል። ይህንንም ተከትሎ የመጀመሪያው አጋማሽ በ ሲዳማ ቡና መሪነት ተጠናቋል።
ከሁለተኛው አጋማሽ በኋላ በሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ እና ተመዛዛኝ በነበረው ጨዋታ ይበልጥ በቁጥር በልጠው ለማጥቃት የሚሞክሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ያገኙትን አጋጣሚ ወደ ግብ ለመቀየር ሲጥሩ ተስተውሏል ነገር ግን ከነዚህ ኳሶች ስህተቶችን በመፈለግ ሲዳማ ቡናዎች ሙከራወችን ለመሰንዘር ሙከራ ሲያደርጉ ተስተውሏል።
78ኛው ደቂቃ ላይ ኢትዮጵያ ቡናዎች እጅግ ለግብ የቀረበን ሙከራን ማድረግ የቻሉ ሲሆን ከመሃል ሜዳ የተሰነጠቀለትን ኳስ ኮንኮኒ ሃፍዝ ተከላካዮችን ወደ እሱ በመሳብ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ዲቫይን ዋቼኩዋ አክርሮ ቢመታውም ግብ ጠባቂው በድንቅ ሁኔታ መልሶበታል። ኢትዮጵያ ቡናዎች ያገኙትን አጋጣሚ በመጠቀም ግብ ለማግኘት ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ጨዋታው በሲዳማ ቡና 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።