በሀያ ስድስተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን የምሽት ጨዋታ አርባምንጭ ከተማን ከስሑል ሽረ አገናኝቶ ጨዋታው ያለ ጎል ተገባዷል።
አዞዎቹ በመቻል ከተሸነፈው ስብስባቸው የሁለት ተጫዋች ለውጥ በማድረግ አንዱዓለም አስናቀ እና አህመድ ሁሴንን አሳርፈው ብሩክ ባይሳ እና ፍቃዱ መኮንን ተክተው ሲገቡ በአንፃሩ ስሑል ሽረዎች ከወልዋሎ ጋር ነጥብ ከተጓሩበት ጨዋታ በሁለት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ነፃነት ገብረመድህን እና ሄኖክ ተወልደን አስቀምጠው መሐመድ ሱሌይማን እና ብርሀኑ አዳሙን በመጀመርያ ተሰላፊነት አስጀምረዋል።
ፌደራል ዳኛ ፍቅሩ ለገሰ ባስጀመሩት የምሽቱ ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጎሎችን ለማስቆጠር ፍላጎት ቢሆኖር በተረጋጋ ሁኔታ ኳሱን ተቆጣጥሮ ክፍት ቦታችን ለመፈለግ የሚደረገው ጥረት ውስንነት የነበረው በመሆኑ በጨዋታው ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች የጠራ የጎል ሙከራዎችን ለመመልከት ተገደን ነበር።
የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ በሄደ ቁጥር የተለየ ነገር ባንመለከትም ኳስ ሲያገኙ በቅብብሎሽ በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃቃቄ ወደ ፊት ለመሄድ የሚያረጉት ሽግግር የጨዋታው መልክ እንዳይደበዝዝ አድርጎታል።
ሆኖም 42ኛው ደቂቃ ላይ ብርሀኑ አዳሙ ከግራ መስመር ወደ ሳጥን የላከው ኳስ ፋሲል አስማማው ሳይጠቀምበት የቀረው እንዲሁም ከሦስት ደቂቃ በኋላ አላዛር ሽመልስ ከቀኝ መስመር በግራ እግሩ ኳሱን አዙሮ በጥሩ ሆኔታ የመታውን የግቡ የግራ ቋሚ የመለሰበት ይሄንኑ ኳስ ብርሀኑ አዳሙ አግኝቶ በቀላሉ ጎል አስቆጠረ ሲባል ግብ ጠባቂው ኢድሪስ ኦጎዶቹ ያመከነበት ስሑል ሽረዎች አጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃ የፈጠሩት ወርቃማ የጎል አጋጣሚዎች ነበሩ ።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ሲመለስ ወደ ፊት በመሄድ ጫና በማሳደር ሽረዎች የተሻሉ የነበረ ሲሆን 53ኛው ደቂቃ አላዛር ሽመለስ ከርቀት ከቅጣት ምት ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ኢድሪስ በቀላሉ ይዞበታል።
የአዞዎቹ አለቃ በረከት ደሙ የሳሳባቸውን የማጥቃት ኃይል ለማጠናከር አንዳርጋቸው መስፍንን እና መሪሁን መስቀለን ቀይረው ቢያስገቡም የታሰበውን ያህል ስኬታማ አልነበሩም።
በተመሳሳይ አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት ኤልያስ አህምድ እና ብሩክ ሀዱሽን ቀይረው ካስገቡ በኋላ 68ኛው ደቂቃ ላይ በቅብሎሽ ኤልያስ አህመድ ያቀበለው አላዛር ሽመለስ በጥሩ ሁኔታ ኳሷን ከፍ አድርጎ የሰጠውን ብሩክ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት የወጣበት ለስሑል ሽረዎች የምታስቆጭ ዕድል ነበረች።
በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች መነቃቃት ያሳዮት አዞዎቹ 80ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር ይሁን እንደሻው ከቅጣት ምት ያሻገረውን አህብዋ ብርያን በግንባሩ የመታውን ግብ ጠባቂው ሞይስ ካዳነበት በኋላ በሁለቱም በኩል ብዙም ተጠቃሽ ነገር ሳይኖር ጨዋታው ያለ ጎል ተጠናቋል።