ዐፄዎቹ እና ብርቱካናማዎቹ የሚያፋልመውና ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ የሚገመተው ጨዋታ 9፡00 ይጀመራል።
ከሦስት ጨዋታዎች የድል ግስጋሴ በኋላ ባሳለፍነው ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና አንድ ለምንም የተረታው ፋሲል ከነማ ወደ ቀደመ ሪትሙ ለመግባት እና ከደረጃ ሰንጠረዡ አካፋይ ዕድገት ለማሳየት ድልን እያሰበ ወደ ሜዳ ይገባል።
ዐፄዎቹ በሁለተኛው ዙር በብዙ መንገድ ተለውጠው ነው የቀረቡት። ቡድኑ ከተከታታይ ድሎቹ ባሻገር በእንቅስቃሴ ረገድ ያሳየው መሻሻል፤ በተለይም የነበረበት የግብ ዕድሎች የመፍጠር ድክመት የቀረፈበት መንገድም ቡድኑን አሻሽሎታል። ቡድኑ በመጨረሻው ጨዋታ ምንም እንኳን ሽንፈት ብያስተናግድም ያሳየው እንቅስቃሴ ግን ለክፉ የሚሰጥ አልነበረም። በአመዛኙ ተመጣጣኝ በነበረው ጨዋታ በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ በርከት ያሉ የግብ ዕድሎች መፍጠር የቻለው ቡድኑ አሁንም ዕድሎች መፍጠር መቀጠሉ በጥሩነቱ የሚጠቀስለት ነጥብ ቢሆንም ከጥድፍያ እና የውሳኔ አሰጣጥ ድክመት ምክንያት ያባከናቸው ዕድሎች ከጨዋታው ነጥብ ይዞ እንዳይወጣ አድርገውታል። ዐፄዎቹ በጨዋታው ከተጋጣሚያቸው የመከላከል አደረጃጀት ጥንካሬ አንፃር ሲለካ በማጥቃቱ በኩል ጥሩ መንቀሳቀሳቸው ባይካድም የአፈፃፀም ድክመታቸው ግን መሻሻል የሚገባው ነው።
በነገው ዕለት ድል የሚቀናቸው ከሆነ በሰንጠረዡ ብያንስ ሁለት ደረጃዎች የማሻሻል ዕድል ያላቸው ዐፄዎቹ ከባለፉት ጨዋታዎች አንፃር ሲታይ
ነገ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ ረገድ ፈታኝ ፍልምያ ይጠብቃቸዋል ተብሎ ይገመታል። በሁለቱም ቡድኖች የአጨዋወት መንገድ መነሻነትም ጨዋታው በመቆጣጠር በኩል ብልጫ የወሰደ ቡድን ጨዋታውን የማሸነፍ የተሻለ ዕድል ይኖረዋል።
ከአስራ አንድ ጨዋታዎች ጥበቃ በኋላ መጠነኛ እፎይታ የሰጣቸውን ድል አዳማ ከተማ ላይ ያገኙት ብርቱካናማዎቹ ከሀድያ ሆሳዕና ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ በኋላ መከናወን የነበረበትን መርሐ-ግብር በዝናብ ምክንያት ከተራዘመ ከ13 ቀናት በኋላ ወደ ጨዋታ ይመለሳሉ።
በሀያ ስድስት ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ብርቱካናማዎቹ ደረጃቸውን የማሻሻል ዕድል የሚሰጣቸው አንድ ቀሪ ጨዋታ ቢኖራቸውም አሁንም ከስጋት ቀጠናው ባለመራቃቸው የነገውን ከባድ ጨዋታ ማሸነፍ ይኖርባቸዋል። ከበላዩ እና ከበታቹ የሚገኙ የቅርብ ተፎካካሪዎቹ መቐለ 70 እንደርታ እና ሀዋሳ ከተማ በመጨረሻው መርሐ-ግብር ድል ማድረጋቸው ተከትሎ ወደ ነገው ጨዋታ ድል በማድረግ ግዴታ ውስጥ ሆኖ የሚገባው ቡድኑ ከአደጋው ቀጠና ለመራቅ ከዚህ ጨዋታ የሚያገኘው ነጥብ በእጅጉ ያስፈልገዋል።
ብርቱካናማዎቹ ሊጉ በአዳማ ከተማ በተካሄደበት ወቅት ድል ሳያደርጉ ከተማውን ቢሰናበቱም በቅርብ ሳምንታት ከውጤቱም ባሻገር ጥሩ ለውጦች አሳይተዋል። በተለይም በአራት ተከታታይ ጨዋታዎች ኳስና መረብ ሳያገናኝ ከዘለቀ በኋላ በ23ኛ እና 24ኛ ሳምንት ጨዋታዎች አራት ግቦች ያስቆጠረው የማጥቃት ክፍል በብዙ ረገድ ተሻሽሏል። ቡድኑ እንደ ከዚህ ቀደም ጨዋታዎች ለመቆጣጠር መቸገሩ እንዲሁም የነገው ተጋጣሚው ጨዋታ በመቆጣጠር ረገድ አወንታዊ ጎኖች ያሉት መሆኑ ምናልባትም ፍልምያውን እንዳያከብድባቸው ያሰጋል፤ ሆኖም የተሻለ የማገገምያ ጊዜ አግኝተው የሚያደርጉት መርሐ-ግብር ከመሆኑ አንፃር ሲታይ ደግሞ ጨዋታው በተሻለ ቅልጥፍና እንዲከውኑ ዕድል ይሰጣቸዋል።
ፋሲል እና ድሬዳዋ በሊጉ እስካሁን 15 ጊዜ ሲገናኙ ሁለቱም ቡድኖች በእኩሌታ ስድስት ስድስት ጨዋታዎች አሸንፈዋል፤ በቀሪዎቹ 3 ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። በጨዋታዎቹ 36 ጎሎች የተቆጠሩ ሲሆን ፋሲል ከነማ 21 ፤ ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ 15 ጎሎች አስመዝግበዋል።