መቻሎች ሽመልስ በቀለ በሁለቱም አጋማሽ ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ታጅበው አዳማ ከተማን 2ለ0 ረተዋል።
አዳማ ከተማ በ25ኛው ጨዋታ ሳምንት በኢትዮጵያ መድን ሽንፈት ካስተናገደበት ቋሚ አሰላለፍ ናትናኤል ተፈራን፣ ፉዓድ ኢብራሂምን ፣ሃይለሚካኤል አደፍረስን እና አሜ መሐመድን አሳርፈው በምትካቸው ዳግም ተፈራ፣ መላኩ ኤልያስ፣ ቻላቸው መንበሩ እና ስንታየሁን መንግስቱን ይዘው ሲቀርቡ መቻል ባሳለፍነው ጨዋታ ሳምንት አርባምንጭ ከተማን ከረታበት ቋሚ ስብስብ ሁለት ለውጥ አድርገው፤ አብዱልከሪም ወርቁ እና ዮዳሄ ዳዊትን አሳርፈው ዮሐንስ መንግሰቱ እና በረከት ደስታን ይዘው ገብተዋል።
ረፋድ ሦስት ሰዓት ተኩል ሲል በጀመረው በዕለቱ መጀመሪያ ጨዋታ መቻሎች ገና ጨዋታ ከመጀመሩ ወደፊት ሮጠው ፈጣን ግብ ለማግባት ሲጥሩ አስተውለናል። የኳስ ቁጥጥር ብልጫን መውሰድ የቻሉት መቻሎች ወደፊት በመሄድ ረግድ ጥሩ የነበሩ ቢሆንም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ በማድረግ አንፃር ደካማ ነበሩ ፤በ6ኛው ደቂቃ ተከላካዩ ፍሪምፖንግ ሜንሱ በመስመር በኩል ሆኖ ያደረገው ሙከራ ኢለማውን ሳይጠብቅ ይቅር እንጂ የመጀመሪያ ለግብ የቀረበ ሙከራ ሆኖ ተመዝግቧል።
አዳማ ከተማ በአንፃራዊነት በረጃጅም ኳሶች ወደ ሦስተኛው ሜዳ ክፍል እየደረሱ የግብ እድል ለመፍጠር ይጣሩ እንጂ ይሄ ነው ተብሎ የሚጠቀስ አጋጣሚ ሳያስመለከቱን ጨዋታው የመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች ሲቆጠሩበት አስቆጪ አጋጣሚ መፍጠር ችለዋል ፤ በተጠቀሰው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት ከተከላካይ ጀርባ የተጣለውን ኳስ ቢኒያም አይተን ብቻውን ይዞ ሳጥን ውስጥ ገብቶ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ አታሎ ለማለፍ ጥረት ሲያደረግ ያመከነው አጋጣሚ ቀዳሚ ሊያደርጋቸው የቀረበ ነበር፤ በዚህ ቅፅበት ተጫዋቹ ግብ ጠባቂውን አታሎ ለማለፍ ሲጥር ፍፁም ቅጣት ይገባኛል ብሎ በመውደቁ የእለቱ ዋና ዳኛ አስመስሎ ወድቋል በሚል ቢጫ ካርድ የመዘዙበት ክስተት ይጠቀሳል።
ጨዋታው ተመጣጣኝ እንቅስቅሴ በሚመስል መልኩ ይቀጥል እንጂ መቻሎች የግብ ማግባት አጋጣሚ ረገድ ብልጫ ነበራቸው። በ22ኛው ደቂቃ ኮሊን ኮፊ ኩጆ ሳጥን ውስጥ ሆኖ ያደረገው ሙከራ ለትንሽ ከግቡ አግዳሚ ርቆ ያለፈበት አደገኛው ሙከራ ቀዳሚ ሊያደርጋቸው የቀረበ ነበር። በተደጋጋሚ ወደ ፊት የነበሩት መቻሎች ቀዳሚ መሆን የቻሉበት ግብ የመጀመሪያው አጋማሽ መደበኛ የጨዋታ ክፍል ተጠናቆ ጭማሪ በታየው ላይ መረብ ላይ አሳርፈዋል። አጋማሹ ሊጠናቀቅ የመጨረሻ ፊሽካ በመጠበቅበት ቅፅበት በረከት ደስታ ከመሃል ሜዳ አከባቢ በረጅሙ የጣለውን ኳስ ሽመልስ በቀለ በግሩም ሁኔታ ተቆጣጥሮ ከመረብ ጋር አገናኝቶ እየመሩ ወደ መልበሻ ክፍል እንዲገቡ አስችሏቸዋል።
ጨዋታው ከእረፍት ተመልሶ አዳማ ከተማዎች የአቻነት ግብ ፍለጋ ጫና ለማድረግ ወደፊት በሚሄዱበት ቅፅበት ተጨማሪ ግብ አስተናግደዋል። በ49ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ነጋሽ በመስመር ከኩል ኳስ ይዞ ገብቶ ያሻማውን ኳስ ሳጥን ውስጥ ብቻውን ሆኖ ሲጠባብቅ የነበረው ሽመልስ በቀለ በደረቱ አቁሞ ድንቅ ግብ አስቆጥሮ መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል። በዚህ ብቻ ያላበቁት መቻሎች በ60ኛው ደቂቃ ላይ ሦስተኛውን ግብ ሁለት ግብ ባስቆጠረው በሽመልስ በቀለ አማካኝነት ለማግኘት ጥረት አድርገዋል።
ሁለተኛ ግብ ካስተናገዱ በኋላ መናቃቃት ያሳዩት አዳማ ከተማዎች በፈጣን ሽግግር ቶሎ ቶሎ ወደፊት እየሄዱ የጦሩን ተከላካይ መስመር መፈተናቸውን ቢያጠናክሩም ጥረታቸው ጠንካራ በሚባል ሙከራ እንዲሁም በጎሎች መታጀብ ግን ሳይችል ቀርቷል። በተለይም ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አሜ መሐመድ አከታትሎ ሙከራውችን ማድረግ ችሎ ነበር 85ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ ሆኖ አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው አልዌንዚ ናፊያን እንዴትም የተቆጣጠረበት ሙከራ ምናልባትም ወደጨዋታው ሊመልሳቸው የሚችል ግብ ለመፍጠር የተቃረበ ጠንካራ ሙከራ ነበር።
ደቂቃው ይበልጥ እየገፋ በሄደ ቁጥር መቻሎች ኳስ ይዘው ወደ እራሳቸው ሜዳ እየመለሱ በእርጋታ ሰዓት ወደ ማምከን ይግቡ እንጂ በመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ለመፍጠር ሙከራ ሲያደርጉ አስተውለናል። 88ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ ሜዳ የገባው ምንይሉ ወንድሙ በመስመር በኩል ሆኖ ያሻማውን ኳስ ሽመልስ በቀለ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ግብ መጥቶ ለጥቂት ባያልፍ ኖሮ መቻሎችን ሦስት ነጥብ ከሦስት ግብ ጋር ፤ ሽመልስ በቀለን ደግሞ ባለ ሀትሪክ ሊያደርገው የቀረበ ነበር። ጨዋታው ወደ መጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሲቃረብ መቻሎች ተጨማሪ ግብ ፍለጋቸውን ቀጥለው የነበረ ቢሆንም ተጨማሪ ግብ ሳያስመለክተን 2ለ0 በሆነ ውጤት ለመቻሎች ሶስት ነጥብ በማጎናፀፍ ተቋጭቷል።