ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ኢትዮጵያ መድን

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ኢትዮጵያ መድን

ወደ ስጋት ቀጠናው የቀረበው ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና በሰንጠረዡ አናት በምቾት የተደላደለው ኢትዮጵያ መድን የሚያደርጉት ጨዋታ ከዚህ ቀደም በግቦች የተንበሸበሸ ግንኙነት ላላቸው አንጋፋ የመዲናይቱ ክለቦች ካለው ወሳኝነት አንፃር ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

የነገውን ሳይጨምር አንድ ቀሪ ጨዋታ እያላቸው በሀያ ዘጠኝ ነጥቦች 13ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከተደቀነባቸው የስጋት ቀጠና ለመውጣት  የሁለተኛው ዙር ጉዟቸውን ማቃናት ግድ ይላቸዋል።

ኤሌክትሪኮች ሁለት ነጥቦች ብቻ ከጣሉባቸው የመጀመርያው ዙር የመጨረሻ አራት ውጤታማ መርሐ-ግብሮች በኋላ ነገሮች በሚፈልጉት መንገድ እየሄደላቸው አይገኝም። በሁለተኛው ዙር በተካሄዱ አምስት ጨዋታዎች ሦስት ሽንፈት፣ አንድ ድል እና አንድ የአቻ ውጤት ማስመዝገቡን ተከትሎ በደረጃ ሰንጠረዡ የተንሸራተተው ቡድኑ ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ድል አድርጎ ከአደጋው ክልል ለመውጣት መሪውን ከሚገጥምበት ጨዋታ ነጥብ ይዞ መውጣት ይኖርበታል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ የቅርብ ተከታዮቹ በቀጣይ መርሐ-ግብሮች ውጤት ከቀናቸው ግን ቡድኑ ይበልጥ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱ አይቀርም፤ ስለዚ ከወትሮ በተለየ ዝግጅት ወደ ጨዋታው መቅረብ ይኖርበታል።

የአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታው ቡድን በቀድሞ የመስመር ጥቃት አስፈሪነቱ አለ ለማለት ባያስደፍርም አሁንም ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ከመድረስ ባለፈ የግብ ዕድሎችን መፍጠር መቀጠሉ በአወንታ የሚነሳለት ነጥብ ነው፤ ከሀዋሳ ከተማ ጋር ነጥብ በተጋራበት ጨዋታ ላይ በተለይም በመጀመርያው አጋማሽ የፈጠራቸው ዕድሎችም የዚህ ማሳያ ናቸው። ሆኖም በነገው ዕለት የሊጉ ጠንካራው የመከላከል ውቅር ያለው ቡድን እንደመግጠሙ ዕድሎች ከመፍጠር አለፍ ብሎ በአፈፃፀሙ በኩልም የተዋጣለት ቀን ማሳለፍ ግድ ይለዋል። ከዚህ በተጨማሪም ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀት ለተጋጣሚው የማጥቃት ጥንካሬ በሚመጥን አኳኋን ወደ ጨዋታው መቅረብ ይጠበቅበታል።

የሊጉ መሪዎች አሁን ላይ በሰንጠረዡ አናት በምቾት ተደላድለዋል፤ በተከታታይ አምስት ጨዋታዎች ሁለት ነጥቦች ብቻ መጣላቸው፤ በጨዋታዎቹ ዘጠኝ ግቦች ማስቆጠራቸው እንዲሁም እየተፈራረቁ የሚከተሏቸው ቡድኖች ነጥብ እየጣሉ መቀጠላቸው እና ነገ ድል ካደረጉ ሊጉን በአስራ አንድ ነጥቦች ልዩነት የመምራት ዕድል ማግኘታቸውም ይህን ለማለት በቂ ነው።

ጉልህ የሆነ የወጥነት ድክመት በሚስተዋልበት ሊግ ላይ ተከታታይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ ለቻምፒዮንነት በሚደረገው ሩጫ ውስጥ ኮስታራ አቋም እንዳላቸው ያሳዩት ኢትዮጵያ መድኖች በቅርብ ሳምንታት ካሳዩት ጥንካሬ አንፃር ከዚህ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ አሳክተው የነጥብ ልዩነቱን ከፍ ለማድረግ ያልማሉ። ቡድኑ ከሚከተለው በኳስ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ አቀራረብ እና ተጋጣሚው በአመዛኙ በሚመርጠው አጨዋወት አንፃር በነገው ጨዋታ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ የማሳካት ዕድሉ ሰፊ ቢሆንም አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በ3ኛ ሳምንት ከመድን ጋር ባደረጉት ጨዋታ ጨምሮ በአንዳንድ ተጠባቂ መርሐ-ግብሮች የተከተሉት ጠጣር አቀራረብ የሚመርጡ ከሆነ ግን ምናልባት ዕድሎች ለመፍጠር እንዲቸገሩ ሊያደርጋቸው ይችላል።

ምንም እንኳን የነገው ተጋጣሚያቸው በአምስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ያስቆጠረ ቡድን ቢሆንም ለወትሮ ግን የተከላካይ ክፍሉ ሁኔታ ለአሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ የሚያሳስባቸው ጉዳይ ነው፤ በ19 ጨዋታዎች 6 ግቦች ብቻ አስተናግዶ በጥንካሬ የዘለቀው የኋላ ክፍሉ ባለፉት 4 ጨዋታዎች ግን 4 ግቦች በማስተናገድ በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ በተከታታይ መረቡን ለማስከበር ተቸግሯል። በቀጣይም ከቀድሞ ብቃቱ አንፃር ሲታይ ውስን ድክመት የታየበትን ክፍል የማሻሻል ስራ መስራት ይኖርባቸዋል።

በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ወደ በጉዳት የሰነበተው በፍቃዱ አስረሳኸኝ ወደ ልምምድ ቢመለስም ለነገው ጨዋታ የማይደርስ ሲሆን ከዚህ ውጭ ያሉ የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ሆነው የሚቀርቡ ይሆናል። በኢትዮጵያ መድን በኩል ጉዳት ላይ ያለው ተከላካዩ ሚሊዮን ሰለሞን ከጉዳቱ ባለማገገሙ በነገው ጨዋታም አይሳተፍም።

ሁለቱ ቡድኖች 27 ጊዜ ተገናኝተው ኤሌክትሪክ 16 ጨዋታ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ኢትዮጵያ መድን 7 ጨዋታዎችን አሸንፏል። በቀሪዎቹ 4 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ለወትሮውም በጎል የታጀበ የእርስ በርስ ግንኙነት ታሪክ ያላቸው ሁለቱ ቡድኖች ባደረጓቸው ጨዋታዎች 2 ጊዜ ብቻ ያለ ጎል ሲያጠናቅቁ ኤሌክትሪክ 42 ፣ መድን 25 ጎሎችን አስቆጥረዋል።