ሊጉ በኢትዮጵያ ዋንጫ ምክንያት ለአስር ቀናት ከመቋረጡ በፊት የሚደረገው መርሐግብር ሐይቆቹ እና ሀምራዊ ለባሾቹን ያፋልማል።
በሃያ አራት ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀዋሳ ከተማዎች በመጨረሻው ጨዋታ ወላይታ ድቻ ላይ ያሳኩት እጅግ አስፈላጊ ድል ደግመው ወደ ወራጅ ቀጠናው መውጫ በር ለመጠጋት ሀምራዊ ለባሾቹን ይገጥማሉ።
በአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምሕረት መሪነት 2ኛውን ዙር ከጀመሩ በኋላ መጠነኛ መነቃቃት አሳይተው ከወራጅ ቀጠናው የመውጣት ዕድላቸው ያለመለሙት ሐይቆቹ በቅርብ ሳምንታት የሚታይ ለውጥ አሳይተዋል። በተለይም በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች በብዙ ረገድ የተሻሻለ እንቅስቃሴ ያሳየው ቡድኑ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወቱን ጥራት ከፍ ማድረጉ ጥንካሬን አላብሶታል።
ቡድኑን ከተረከቡበት ወቅት ጀምሮ ቀጥተኛነትን በተላበሰ መልኩ በቶሎ ወደ ጎል የሚደርስ አጨዋወት እየተከተሉ የሚገኙት አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምሕረት ነገም የአቀራረብ ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ ተብሎ ሲገመት አራት ነጥብ ባሳኩባቸው ሁለት መርሐ-ግብሮች ላይ የሚገኙትን የግብ ዕድሎች የመጠቀም ውስንነት የታየበት የፊት መስመራቸውን ስል ማድረግ ይኖርባቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም ባለፉት መርሐ-ግብሮች ኳሱን ለመቆጣጠር እምብዛም ፍላጎት ያላሳየው የአማካይ ክፍል በነገው ዕለት ጠንካራ የአማካይ ጥምረት ካላቸው የሊጉ ክለቦች አንዱ የሆነውና ጨዋታን በመቆጣጠር አወንታዊ ጎን ያለው ቡድን እንደመግጠሙ በቀላሉ በተጋጣሚ የአማካይ ክፍል እየተዋጠ የመጨረሻ ኳሶችን ለማድረስ እንዳይቸገር የመሀል ክፍሉን በቶሎ የማከም አጣዳፊ ኃላፊነት ይኖርባቸዋል።
ከበላያቸው የተቀመጠው መቐለ 70 እንደርታ ዛሬ ሽንፈት ማስተናገዱን ተከትሎ የነጥብ ልዩነቱን የሚያጠቡበት ዕድል ያገኙት ሐይቆቹ ወደ ወራጅ ቀጠናው መውጫ በር ላይ ከተቃረቡበት እና ወሳኝ ድል ካሳኩበት ማግስት የሚያሳዩት የመንፈስ ንቃትም ከቡድኑ የሚጠበቅ ነው።
በሰላሣ አምስት ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በመጨረሻው ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ የተቀዳጁትን ድል ነገ መድገም የሚችሉ ከሆነ ሁለት ደረጃዎች በማሻሻል ወደ ዋንጫ ፉክክሩ የሚጠጉበት ዕድል ያገኛሉ።
ሀምራዊ ለባሾቹ በ2ኛው ዙር በብዙ መንገድ ተሻሽለው በመቅረብ የውድድር ዓመቱ ጉዟቸው አቃንተዋል፤ ሁለተኛው የውድድር መንፈቅ ከተጀመረ በኋላ በተካሄዱ ስድስት ጨዋታዎች አራት ድል፣ አንድ ሽንፈት እና አንድ የአቻ ውጤት ያስመዘገበው ቡድኑ በላይኛው የሰንጠረዡ ክፍል ባለው ፉክክር ለመሳተፍ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ከሚጠበቀው የነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማግኘት ይኖርበታል፤ ይህ እንዲሆን ግን ቡድኑ በርከት ባሉ ጉዳዮች መሻሻል ይኖርበታል። ቀዳሚው የሚገኙ የግብ ዕድሎች በመፈፀም ረገድ የሚታየው ክፍተት ነው። ቡድኑ ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ማስቆጠር ቢችልም ፈረሰኞቹን ባሸነፈበት ጨዋታ ጨምሮ ቀድመው በተካሄዱ መርሐ-ግብሮች ዕድሎች በመጠቀም ረገድ የነበረው ጥንካሬ ግን አጥጋቢ አልነበረም። የተጠቀሰው ድክመትም በመጨረሻው መርሐ-ግብር እንደታየው ቡድኑ በጨዋታ መገባደጃ ደቂቃዎች ውጤት ለማስጠበቅ ጫና ውስጥ እንዲገባ እያደረገው ስለሚገኝ ድክመቱን ማረም አለበት። ከዚህ በተጨማሪ ቅዱስ ጊዮርጊስን በረቱበት ጨዋታ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ የተጋጣሚን መልሶ ማጥቃቶች ለማቆም ጫና ውስጥ ሲገባ የተስተዋለው የተከላካይ ክፍሉ በነገው ዕለት በርከት ያሉ የመልሶ ማጥቃት መሳርያዎች ያሉት ቡድን እንደመግጠሙ ከወትሮ ለየት ባለ ጥንቃቄ ጨዋታውን መከወን ግድ ይለዋል።
በሀዋሳ ከተማ በኩል በአወዳዳሪው አካል ከታገደው አጥቂው እስራኤል እሸቱ ውጪ ሁሉም የቡድን አባላት ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው። በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ተከላካዩ ካሌብ አማንክዋህ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጭ ነው። ፈቱዲን ጀማል እና አዲስ ግደይም ወደ ልምምድ የተመለሱ ቢሆንም የመጫወታቸው ጉዳይ ግን በአሰልጣኙ ውሳኔ የሚታወቅ ይሆናል። የተቀሩ የቡድኑ አባላት ግን ለጨዋታው ዝግጁ መሆናቸው ታውቋል።
በሊጉ 38 ጨዋታዎች የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች በ13 ጨዋታዎች ነጥብ በመጋራት ሲፈፅሙ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ15 እንዲሁም ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ በ10 ጨዋታዎች ድል ማድረግ ችለዋል። በጨዋታዎቹ ንግድ ባንኮች 42፤ ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ 37 ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።