ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድን ወሳኝ ድል አሳክቷል

ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድን ወሳኝ ድል አሳክቷል

በመሐመድ አበራ ሁለት ጎሎች ኢትዮ ኤሌክትሪክን የረቱት ኢትዮጵያ መድኖች ሊጉን በአስራ አንድ ነጥብ ልዮነት እንዲመሩ አስችሏቸዋል።


ኢትዮ ኤሌክትሪክ ባሳለፍነው ሳምንት ከድሬደዋ ከተማ ጋር መጫወት የነበረበትን ጨዋታ በዝናብ ምክንያት ካለማድረጉ በፊት በ24ኛ ሳምንት ከሀዋሳ ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋራበት ስብስቡ  ምንም አይነት የተጫዋች ለውጥ ያላደረገ ሲሆን የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን በበኩሉ አዳማ ከተማን ያሸነፈበትን ስብስብ በተመሳሳይ ለውጥ ሳያደርግ ለጨዋታው ቀርቧል።

ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሀይለየሱስ ባዘዘው በመሩት በዚህ ጨዋታ ሙከራዎችን በማድረግ በኩል የተቀዛቀዘ የሚመስለው የሁለቱ ቡድኖች የጨዋታ ጅማሮ ኳስ ሲያገኙ ሜዳውን አስፍተው በፈጣን እንቅስቃሴ ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ለመጠጋት የሚያደርጉት ፍሰት ያለው የማጥቃት እንቅስቃሴ  ጨዋታውን ተመጣጣኝ ፉክክር እንዲኖረው አድርጎት ዘልቋል።

ሆኖም ቀስ በቀስ አንዳቸው ጎል ማስቆጠር ወደ የሚችሉበት አጋጣሚ ይገባሉ ቢባልም የጠራ የጎል ዕድሎችን የተመለከትነው በሁለት አጋጣሚ ነው። 22ኛው ደቂቃ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከማዕዘን ምት የተገኘውን ኳስ ሄኖክ ገብረህይወት በግንባሩ ገጭቶ ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ ያወጣበት እንዲሁም በ36ኛው ደቂቃ በኢትዮጵያ መድኖች በኩል በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ በረከት ካሌብ ከቀኝ መስመር የላከውን አጥቂው አለን ካይዋ በጥሩ ዝላይ በግንባሩ የመታውን ግብ ጠባቂው ኢድሪሱ ንቁ ሆኖ የያዘበት ለማግባት የተቃረቡበት አጋጣሚ ነበር።

በአጋማሹ መግቢያ ላይ የኳስ ቁጥጥሩን የበላይነት የወሰዱት የሊጉ መሪ መድኖች ያሬድ ካሳይ ከግራ መስመር የጣለለትን መሐመድ አበራ ነፃ ኳስ አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቶ ጨዋታው ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።  ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ 49ኛው ደቂቃ የኢትዮ ኤሌክሪኩ ግብ ጠባቂ ኢድሪሱ በእግር ማራቅ የነበረበትን ኳስ በእጁ መያዙን ተከትሎ የተሰጠውን ሁለተኛ ቅጣት ምት ሀይደር ያሻገረለትን ያሬድ ካሳይ በግንባሩ አግኝቶ ለጥቂት በወጣበት ሙከራ ጨዋታው ተነቃቅቶ ተጀምሯል።

ኤሌትሪኮች ወደ ራሳቸው ሜዳ ተጠግተው ኳስ ሲያገኙ በመልሶ ማጥቃት ጥቃት ለመሰንዘር ሲያስቡ በአንፃሩ መድኖች በሁሉም የሜዳ ክፍሎች ክፍት ቦታን ፈልጎ ጎል ለማስቆጠር በሚደረግ ጥረት ጨዋታው ተጋግሎ  ቀጥሎ በ56ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ የገባው ኢዮብ ገብረማርያም በግራ እግሩ አክሮ የመታውን ኳስ ግብጠባቂው አቡበከር አምክኖበታል።

75ኛው ደቂቃ ላይ ኢትዮጵያ መድኖች መሪ የሆኑበትን ጎል ከፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥረዋል ፤ ሀይደር ሸረፋ ከግራ መስመር ጠርዝ ያሻገረለትን አቡበከር ሳኔ ኳሱን ለማለፍ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ያሬድ የማነ ጠልፎታል በሚል የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት መሐመድ አበራ ወደ ጎልነት ቀይሮት ቡድኑን መሪ አድርጓል።



በቀሪ ደቂቃዎች ኢትዮ ኤሌትሪኮች ጫና ለመፍጠር ቢጥሩም ከማፈግፈግ ይልቅ ኳስ ነጥቀው ይወጡ የነበሩት መድኖች ጨዋታውን በመቆጣጠር 87ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ጎላቸውን ማግኘት ችለዋል። ያሬድ ካሳይ በጥሩ ሁኔታ ከግራ መስመር ጠርዝ ያቀበለውን መሐመድ አበራ በአስደናቂ ሁኔታ በግንባሩ ገጭቶ ኳሱን ግብ ጠባቂው ኢድሪሱ መረብ ላይ አሳርፎታል። በየጨዋታዎቹ ጎል በማስቆጠር በድንቅ አቋም ላይ የሚገኘው አጥቂው መሐመድ አበራ የዛሬው ሁለት ጎሎች ጨምሮ ያስቆጠራቸውን የጎል መጠን አስር ሆኖ ተመዝግቦለታል ፤ ጨዋታውም በኢትዮጵያ መድን 2-0 አሸናፊነት ተቋጭቷል።