ሀዋሳ ከተማዎች ከመመራት ተነስተው በኤርትራዊው ዓሊ ሱሌይማን ግቦች ታግዘው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 2-1 በማሸነፍ በውድድር ዓመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ተከታታይ ድል አሳክተዋል።
በ26ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ባለ ሜዳውን ሀዋሳ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ያገናኘው ጨዋታ የሳምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር ነበር። ሀዋሳ ከተማዎች ባሳለፍነው ሳምንት ከወላይታ ድቻ ጋር የነበራቸውን ጨዋታ 1-0 በሆነ ውጤት ድል ሲያደርጉ እንዲሁም ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ያሳኩትን ድል ለመድገም ወደ ሜዳ ገብተዋል።
በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥሩ እና ተመጣጣኝ የሆነ የኳስ እንቅስቃሴ ሲኖረው በሁለቱም በኩል ፈጣን በሆነ ሽግግር ወደ ግብ መድረስ የቻሉ ሲሆን 16ኛው ደቂቃ ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ከግራ መስመር በኩል ያገኙትን የቅጣት ምት ሱሌይማን ሀሚድ ቀጥታ በመምታት ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከግቡ መቆጠር በኋላ የአቻነት ግብ ለማግኘት ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት ሀዋሳ ከተማዎች ፈጣን በሆኑ ሽግግሮች የንግድ ባንኮችን የግብ ክልል ደጋግመው መጎብኘት ችለዋል። 37ኛው ደቂቃ ላይ ከፍተኛ የሆነ የጎል ፍላጎት የነበራቸው ሀዋሳ ከተማዎች ቢኒያም በላይ ከመሀሉ የሜዳ ክፍል ወደ ግራ መስመር በመሆን በድንቅ ዕይታ ያሻገረውን ኳስ ኤርትራዊው ዓሊ ሱሌይማን ጥሩ በሆነ የመጀመሪያ ንክኪ አመቻችቶ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን አቻ አድርጓል። በዚህም የመጀመሪያው አጋማሽ ያለ ተጨማሪ ግቦች 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
ከዕረፍት መልስ ይበልጥ ግብ ለማስቆጠር ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት ሀዋሳ ከተማዎች 49ኛው ደቂቃ ላይ ቸርነት አውሽ ከመሀል ሜዳ በመነሳት እያታለለ ይዞ በመምጣት የሰጠውን ኳስ ያገኘው ዓሊ ሱሌይማን ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ በመሆን የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን ድንቅ በሆነ ጥረት ጨርፎ ወደ ውጭ አስወጥቷታል።
ከነዚህ ደቂቃዎች በኋላ በሁለቱም ቡድኖች መካከል ጥሩ የሆነ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎችን የተመለከትን ሲሆን ኳሶች ፈጣን በሆነ ሽግግር ወደ ፊት ያለ መቆራረጥ ይደርሱ ነበር ይሄም ለተመልካች እጅግ ሳቢ እና ማራኪ አድርጎት ነበር። በጣም ጥሩ እንቅስቃሴን ሲያስመለክቱን የነበሩት ሐዋሳ ከተማዎች 80ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ታፈሰ ሰለሞን ድንቅ በሆነ እይታ ሰንጥቆ ያቀበለውን ኳስ ዓሊ ሱሌይማን የግል ችሎታውን ባሳየበት አጨራረስ ለራሱ እና ለክለቡ ሁለተኛ ግብ በማስቆጠር ሜዳ ውስጥ የነበሩትን ደጋፊዎች በደስታ ስሜት እንዲዋጡ አድርጓል። ይህንንም ተከትሎ በአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት የሚመሩት ሀዋሳ ከተማዎች 2-1 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል።