ምዓም አናብስት የ የአብሥራ ተስፋዬን ጉዳይ ወደ ዓለም አቀፉ የስፖርት ገላጋይ ፍርድ ቤት ወስደውታል።
ለተጫዋች የአብስራ ተስፋዬ የቅድመ ክፍያ ብር ከፍላችኋል በሚል በፕሪሚየር ሊግ ሼር ካምፓኒ የፋይናንስ አሰራር ተቆጣጣሪ ኮሚቴ የቅጣት ውሳኔዎች የተላለፈበት እና የኢ.እ.ፌ የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ውሳኔውን ያፀናበት መቐለ 70 እንደርታ ስፖርት ክለብ ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፉ የስፖርት ገላጋይ ፍርድ ቤት (ካስ) ወስዶታል።
በፋይናንስ አሰራር ተቆጣጣሪ ኮሚቴ የተወሰነበትን ቅጣት እና የኢ.እ.ፌ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ያፀናውን ውሳኔዎች “ካለ አግባብ ያለጥፋቴ የተወሰኑብኝ ውሳኔዎች ናቸው።” በማለት ውሳኔዎቹን በመቃወም ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፉ የስፖርት ገላጋይ ፍርድ ቤት (ካስ) ይዞ በመሄድ ይግባኝ የጠየቀው ክለቡ ማስረጃዎች፤ አጋዥ ዶክመንቶችና መሟገቻ ነጥቦች የላከ ሲሆን በዛሬው ዕለትም ይግባኙ በካስ ተቀባይነት እንዳገኘ እና ሂደቱ በቅርቡ እንደሚጀመር ለማወቅ ተችሏል።
እንዲሁም ክለቡ በይፋዊ ገፁ ባሰፈረው መግለጫ
‘ካስ’ የይግባኙን ጉዳይ መርምሮ ተገቢውን የመጨረሻ ውሳኔ እስኪያስተላልፍ ድረስ በክለቡና በተጫዋቹ ላይ የተላለፉትን ቅጣቶች ተፈፃሚ እንዳይሆኑ እና ታግደው እንዲቆዩ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጿል።