የኢትዮጵያ ዋንጫ መረጃዎች | ሸገር ከተማ ከ ወላይታ ድቻ

የኢትዮጵያ ዋንጫ መረጃዎች | ሸገር ከተማ ከ ወላይታ ድቻ

ወደ ፍጻሜው የሚያልፈውን አንድ ቡድን የሚለየውን የግማሽ ፍጻሜ ቀዳሚ ጨዋታ አስመልክተን ያሰናዳናቸውን መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

ክለቦች ውህደት ፈጥረው ከመሰረቱት በኋላ በሁለተኛው ዓመቱ አስደናቂ ዓመት አሳልፎ ወደ ፕሪምየር ሊጉ መግባቱ ያረጋገጠው ክስተቱ ሸገር ከተማ በከፍተኛ ሊጉ ያሳካውን ድል በኢትዮጵያ ዋንጫውም ለመድገም የጦና ንቦቹን ይገጥማል።

በአሰልጣኝ በሽር አብደላ የሚመራው ሸገር ከተማ በፕሪምየር ሊጉ ብርቱ ተፎካካሪ የሆኑትን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ባህር ዳር ከተማን በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍፃሜው የደረሰ የከፍተኛ ሊጉ ብቸኛ ተወካይ ነው። ቦሌ ክፍለ ከተማን ሦስት ለሁለት በማሸነፍ ውድድሩን የጀመረው ቡድኑ በቀጣዮቹ ዙሮች ብርቱ ተፎካካሪዎችን ረቶ ወደዚህ መድረክ የበቃ  እንደመሆኑ ቀላል ግምት አይሰጠውም። ሆኖም በነገው ዕለት በመጨረሻዎቹ ሰባት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በአምስቱ መረቡን አስከብሮ የወጣውን ቡድን እንደመግጠማቸው የፊት መስመራቸውን ይበልጥ ማጠናከር ይኖርባቸዋል።

ወላይታ ድቻዎች ባለፈው ዓመት እስከ ፍጻሜው ደርሰው ያላሳኩትን ዋንጫ ለማግኘት በግማሽ ፍጻሜው ሸገር ከተማን ይገጥማሉ።

መቐለ 70 እንደርታን በመለያ ምት በማሸነፍ የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታቸው የጀመሩት ወላይታ ድቻዎች በቀጣይ ዙር ቦዲቲ ከተማን ፣ በሩብ ፍጻሜው ደግሞ ሀዋሳ ከተማን በመለያ ምት በማሸነፍ ነው ለግማሽ ፍጻሜው የበቁት።

ባለፈው የውድድር ዓመት በተመሳሳይ መድረክ አስር ግቦች ማስቆጠር ችለው የነበሩት የጦና ንቦቹ ዘንድሮ ያስቆጠሩት የግብ መጠን ግን ሦስት ብቻ ነው። በፕሪሚየር ሊጉ የነበራቸው የተከታታይ ድሎች ጉዞ ማስቀጠል ያልቻሉት የጦና ንቦች የግብ ማስቆጠር ድክመት በታየባቸው የመጨረሻዎቹ ሦስት የሊግ ጨዋታዎች ያስቆጠሩት የግብ መጠንም አንድ ብቻ ነው። የቡድኑ የግብ ማስቆጠር ችግርም ከወዲሁ መፈታት የሚገባው ድክመት ነው።

በሸገር ከተማ በኩል አመንቲ አቢቲ በቅጣት ምክንያት የነገው ጨዋታ የሚያመልጠው ሲሆን ሌሎቹ የቡድኑ አባላት ግን ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው። በወላይታ ድቻ በኩል ጉዳት ላይ የነበሩት ናትናኤል ናሴሮ እና ውብሸት ክፍሌ ከጉዳት አገግመው ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ሆነዋል።

የነገውን ጨዋታ ፌዴራል አልቢትር ዳንኤል ይታገሱ ይመሩታል።