የኢትዮጵያ ዋንጫ | የጦና ንቦቹ ለተከታታይ ዓመት የፍፃሜ ተፋላሚ መሆናቸውን አረጋገጡ

የኢትዮጵያ ዋንጫ | የጦና ንቦቹ ለተከታታይ ዓመት የፍፃሜ ተፋላሚ መሆናቸውን አረጋገጡ

በኢትዮጵያ ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ መርሃግብር ሸገር ከተማን የገጠመው ወላይታ ድቻ 2ለ0 በመርታት ለሁለተኛ ተከታታይ ዓመት የፍፃሜ ተፋላሚ መሆኑን አረጋግጧል።


በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ለመወከል የፍፃሜ ተፋላሚ ሆኖ ለመገኘት ጨዋታቸውን ያደረጉት ሸገር ከተማ እና ወላይታ ድቻ 9፡30 ሲል በፌድራል ዋና ዳኛ ዳንኤል ይታገሱ እየተመሩ መርሀግብራቸውን አከናውነዋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ በይበልጥ ከመስመር መነሳትን መርጠው በመንቀሳቀስ በተጋጣሚያቸው ላይ ሙሉ ብልጫ የነበራቸው ወላይታ ድቻዎች 4ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር መሳይ ሠለሞን ከተከላካዮች ጋር ታግሎ የሰጠውን ኳስ ፀጋዬ ብርሀኑ ሲመታው የግብ ዘቡ አቤል በላይ ጥረት ታክሎበት ኳሷ ወደ ውጪ ወጥጣለች።

ለተጋጣሚያቸው የንክኪ አጨዋወት ነፃነትን የፈቀዱት ሸገሮች በፀጋዬ ብርሀኑ ከተደረገባቸው ሙከራ መልስ 39ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አስተናግደዋል። በጥሩ ንክኪ መሳይ ያመቻቻትን ኮስ ፀጋዬ በቀጥታ መቶ ግብ ጠባቂው ሲመልሳት ጎሉ ስር ያመራችውን ኳስ ያገኘው ዘላለም አባተ በግንባር ገጭቶ ከመረብ በማሳረፍ ወላይታ ድቻን መሪ አድርጓል።

ከዕረፍት መልስ መጠነኛ መሻሻሎችን በእንቅስቃሴያቸው ቢያስመለክቱንም የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የድቻዎች የኋላ መስመር ፈተና የሆነባቸው ሸገሮች 51ኛው ደቂቃ ላይ ሌላ ተጨማሪ ጎል ተቆጥሮባቸዋል።

ዘላለም አባተ ከጥሩ ቅብብል በኋላ ከግራ ወደ ውስጥ ያሻገራትን ኳስ መቆጣጠር ተስኖት ግብ ጠባቂው አቤል በላይ የተፋትን ኳስ ያገኘው ብዙአየሁ ሰይፈ ወደ ጎልነት በመለወጥ የጦና ንቦቹን ወደ 2ለ0 ከፍ አድርጓል። ሁለት ጎሎችን ካስተናገዱ በኋላ በመልሶ ማጥቃት ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረትን ሲያሳዩን የታዩት ሸገሮች በተቃራኒው ወደ መጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በወላይታ ድቻ በኩል ያሬድ ዳርዛ በሁለት አጋጣሚ ሁለት ግልፅ ኳሶችን ካባከነ በኋላ በመጨረሻም ጨዋታው በወላይታ ድቻ 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ክለቡም በፍፃሜ መርሀግብር የሲዳማ እና መቻል ተጋጣሚ ይገጥማል።

የኢትዮጵያ ዋንጫ ሌላኛውን የፍፃሜ ተፈላሚን የሚለየው የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ነገ ዕሁድ ዘጠኝ ሰአት ከሰላሳ ሲል ሲዳማ ቡናን ከመቻል ጋር የሚያፋልም ይሆናል።