ሲዳማ ቡና በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ዋንጫ ፍፃሜ ጨዋታ ለማለፍ፡ 13 ዋንጫዎች በማንሳት ባለ ‘ሪከርድ’ የሆነው መቻል ደግሞ ከ 7 ዓመታት በኋላ ወደ ፍፃሜ ለመብቃት የሚፋለሙበት ጨዋታ ወላይታ ድቻን ተከትሎ ወደ ፍፃሜው የሚያልፍ ቡድን ይለይበታል።
በፕሪምየር ሊጉ ከአምስት ድል አልባ የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ሦስት ተከታታይ ድሎች አስመዝግበው ደረጃቸውን ያሻሻሉት ሲዳማ ቡናዎች በሊጉ ያሳዩት መነቃቃት በኢትዮጵያ ዋንጫ በማስቀጠል ወደ ፍፃሜው ለማለፍ መቻልን ይገጥማሉ።
ሶሎዳ ዓድዋን በመለያ ምት አሸንፈው የኢትዮጵያ ዋንጫ ውድድራቸውን የጀመሩት ሲዳማ ቡናዎች በጉዟቸው ስሑል ሽረን አንድ ለባዶ፤ በግማሽ ፍፃሜው ደግሞ ሀድያ ሆሳዕናን ሦስት ለባዶ በማሸነፍ ነው ወደ ነገው የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ የሚቀርቡት። ሲዳማ ቡናዎች በፕሪምየር ሊጉ ዝቅተኛ የግብ መጠን በማስመዝገብ 3ኛ ደረጃ ላይ ቢቀመጡም በኢትዮጵያ ዋንጫ ግን ጥሩ የግብ ማስቆጠር ንፃሬ አላቸው። በውድድሩ በጨዋታ በአማካይ ሁለት ግቦች በማስቆጠር ወደ እዚህ መድረክ የበቃው ቡድኑ በነገው ዕለትም ይህንን ጥንካሬውን ማስቀጠል ይኖርበታል። ተጋጣሚው መቻል በውድድሩ ባደረጋቸው 3 ጨዋታዎች 1 ግብ ብቻ ያስተናገደ እንዲሁም በመጨረሻዎቹ 3 የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ መረቡን ያላስደፈረ መሆኑ ግን ፈተናው ከባድ ያደርግበታል።
አዲስ አበባ ከተማን አራት ለባዶ፤ ሱሉልታ ክፍለ ከተማን ሁለት ለባዶ በግማሽ ፍፃሜው ደግሞ የፕሪምየር ሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድንን ሦስት ለአንድ በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍፃሜው የበቁት መቻሎች ከ 7 ዓመታት በኋላ የለመዱትን ዋንጫ ለመሳም ከሲዳማ ቡና ጋር ይፋለማሉ።
መቻል በፕሪምየር ሊጉ ከዘጠኝ የውጣ ውረድ ሳምንታት በኋላ ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ድል አድርጎ አለሁ ብሏል፤ ድሎቹን ተከትሎ በሊጉ ደረጃውን ያሻሻለው ቡድኑ በሒሳባዊ ስሌት ገና ቢሆንም ከመሪው በ13 ነጥቦች ርቀት ላይ እንደመገኘቱ ዓመቱን ካለ ዋንጫ ለማጠናቀቅ በኢትዮጵያ ዋንጫ መበርታት ይኖርበታል። በውድድሩ በተከናወኑ ሦስት ጨዋታዎች ዘጠኝ ግቦች በማስቆጠር ፊት የተቀመጠው የአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራው ቡድን በማጥቃቱ ብቻ ሳይሆን በመከላከሉም ጠንካራ ነው፤ ጦሩ በኢትዮጵያ ዋንጫ በተከናወኑ ሦስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ማስተናገዱ እንዲሁም ጥሩ ተንቀሳቅሶ ዘጠኝ ነጥብ ባፈሰባቸው የመጨረሻ ሦስት የሊግ መርሐ-ግብሮች መረቡን አስከብሮ መውጣቱ የተከላካይ ክፍሉ ወቅታዊ ብቃት ማሳያ ነው። ሆኖም በነገው ዕለት ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ሳይቆጠርበት ድል ያደረገው እና በጥሩ የማሸነፍ መንፈስ የሚገኘው ቡድን እንደመግጠሙ የሚጠብቀው ፈተና ከባድ እንደሚሆን እሙን ነው።
ከውድድር ዓመቱ መጀመር በፊት የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ቅድመ ግምት የተሰጣቸው ሁለቱም ቡድኖች ዓመቱን ካለ ዋንጫ ለማጠናቀቅ የሚያደርጉት ፍልምያ እንደመሆኑ ለሁለቱም በተመሳሳይ ወሳኝ ነው፤ ከዚህ በተጨማሪ ሁለቱም ቡድኖች የመጨረሻዎቹ ሦስት የሊግ ጨዋታዎች ድል ማድረጋቸው፤ በጨዋታዎቹ መረባቸውን ማስከበራቸው እንዲሁም በብዙ መለክያዎች በተመሳሳይ ወቅታዊ ብቃት ላይ ሆነው ወደ ነገው ወሳኝ ጨዋታ መቅረባቸው መርሐ-ግብሩ ተጠባቂ ያደርገዋል።
በነገው ወሳኝ መርሐ-ግብር በሲዳማ ቡና በኩል በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ሦስት ወሳኝ ግቦች ያስቆጠረው ፍቅረየሱስ ተ\ብርሀን በመቻል በኩል ደግሞ በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች አራት ወሳኝ ግቦች ያስቆጠረው ሽመልስ በቀለ ይጠበቃሉ።
ሲዳማ ቡና በአምስት ቢጫ ወሳኝ ተጫዋቾቹ የሆኑት ግብ ጠባቂውን ቶማስ ኢካራ እና አጥቂው ሀብታሙ ታደሰን ሲያጣ ከሰሞኑ ከአስራ ስምንት ውጭ ይሆን የነበረው ይገዙ ቦጋለ ግን ለነገው ጨዋታ እንደሚመለስ ሰምተናል። ከዚህ ውጭ ሁሉም የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።
በመቻል በኩል ዮሴፍ ታረቀኝ ከጉዳት መመለሱ ሲታወቅ ባሳለፍነው ሳምንት በተደረገ የሊግ ጨዋታ (ከአዳማ ከተማ ጋር) የነገውን ወሳኝ ፍልሚያ ታሳቢ በማድረግ ከካርድ እና ጉዳት ለመጠበቅ እረፍት ተሰጥቶት የነበረው አብዱልከሪም ወርቁ ነገ ወደ ሜዳ እንደሚመለስ ታውቋል። ይህንንም ተከትሎ ሁሉም የቡድኑ ተጫዋቾች ለጨዋታው ዝግጁ እንደሆኑ ተመላክቷል።
መቻል 12 ዋንጫዎች ካነሳው ቅዱስ ጊዮርጊስ በአንድ ልቆ 13 ዋንጫ በማንሳት የውድድሩ ባለ ሪከርድ ነው፤ በ2010 ቅዱስ ጊዮርጊስን በመለያ ምት ረቶ ያሸነፈው ዋንጫም የመጨረሻው ነበር፤ ሲዳማ ቡና ግን በውድድሩ ዋንጫ የማንሳትም ሆነ ወደ ፍፃሜው ጨዋታ የመሻገር ታሪክ የለውም።