በዝናብ እና መብራት ምክንያት ሁለት ጊዜ ተራዝሞ ዛሬ ረፋድ ላይ በተቋጨው ጨዋታ ኤሌክትሪክ ድሬዳዋን 2ለ0 አሸንፏል።
25ኛ ሳምንት ላይ ሊደረግ ቀጠሮ ተይዞለት በዕለቱ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት የተራዘመው የድሬዳዋ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታ በተስተካካይ መርሐግብር ትናንት እና ዛሬ ተደርጓል። ሁለቱም ቡድኖች ከተደቀነባቸው ከሊጉ የመውረድ አደጋ ሶስት ነጥብ በማሳካት ራሳቸውን ነፃ ለማድረግ የሚደረግ ጨዋታ ስለነበር ለሁለቱም ቡድኖች እጅግ ወሳኝ ትኩረት የተደረገበት ጨዋታ ነበር።
ተጠባቂውን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ በፊሽካቸው ያስጀመሩት ሲሆን የመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በአመዛኙ በቅብብሎሽ የጨዋታውን ብልጫ መቆጣጠር የቻሉ ሲሆን የመጀመሪያዎቹን 15 ደቂቃዎች በጨዋታ እና በግብ እንቅስቃሴ ድሬዳዋ ከተማዎች የተሻሉ ነበሩ። የቀሩትን ደቂቃዎች በፈጣን ሽግግር ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ብልጫ መውሰድ ችለዋል።
በፈጣን ሽግግሮች ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል በብዛት የሚገቡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች 33ኛው ደቂቃ ላይ የድሬዳዋ ከተማው አብዱልሰላም የሱፍ የኤሌክትሪኩ አቤል ሀብታሙ ላይ በሰራው ጥፋት ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት ሽመክት ጉግሳ ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
የድሬዳዋ ከተማ አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ጨዋታው ወደ ዕረፍት ሊያመራ በተሰጠው ጭማሪ ደቂቃ ውስጥ ከዕለቱ ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት በቀይ ካርድ ከሜዳ ሲሰናበት የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቅቆ ወደ መልበሻ ክፍል ሲያመሩም ሌሎች ንትርኮች እንደነበሩ ተመልክተናል።
ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ራሳቸውን አሻሽለው የቀረቡት ድሬዳዋ ከተማዎች በኳስ ቁጥጥሩ እና በእንቅስቃሴ ረገድ የተሻሉ ሁነው መቅረብ የቻሉ ሲሆን በቁጥር በዛ በማለት ከመስመር ከሚነሱ ኳሶች የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ተስተውሏል። ጨዋታው ረዘም ያሉ ደቂቃዎችን በድሬዳዋ ከተማዎች ብልጫ በመውሰድ የአቻነት ግብ ለማግኘት ጥረት ቢያደርጉም ነገርግን 81ኛው ደቂቃ ላይ ጥረታቸውን መና ያስቀረ ግብ ተቆጥሮባቸዋል። ከጎሉ ርቀት ላይ የተሰጠውን ቅጣት ምት አሸናፊ ጥሩነህ ድንቅ የሆነ ቅጣት ምት በማስቆጠር መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል።
87ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ የስታዲየሙን መብራት የሚያበራ ሰው ባለመኖሩ ጨዋታው ከትናንት ወደ ዛሬ ረፋድ 3፡30 ተራዝሞ ዛሬ በተቋጩት የመጨረሻ ደቂቃዎች ድሬዳዋ ከተማዎች አጥቅተው ለመጫወት ጥረት ቢያደርጉም ሱራፌል ጌታቸው ካደረገው ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ውጪ ቻርለስ ሙሴጌን ዒላማ ያደረጉ ኳሶች ግባቸውን ሳይመቱ ቀርተው ጨዋታው በኢትዮ ኤሌክትሪክ 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።