ድሬዳዋ ከተማ በደል ተፈፅሞብኛል በማለት የቅሬታ ደብዳቤ አስገብቷል

ድሬዳዋ ከተማ በደል ተፈፅሞብኛል በማለት የቅሬታ ደብዳቤ አስገብቷል

በዝናብ እና መብራት ሦስት ቀናቶችን ፈጅቶ ትናንት በተጠናቀቀው የድሬዳዋ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታ ዙሪያ ድሬዳዋ ከተማ በዕለቱ ዳኛ የውጤት ማስቀየር ተፈፅሞብኛል ይጣራልኝ ሲል በደብዳቤ ጠይቋል።

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በ25ኛ ሳምንት ሊደረግ የነበረው የድሬዳዋ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታ ሀዋሳ ላይ ጥሎ በነበረው ከባድ ዝናብ ምክንያት የቀን መራዘም ተደርጎበት ከትላንት በስቲያ አመሻሽ 11 ሰዓት ላይ ተደርጎ በትናንትናው ዕለት መቋጨቱ ይታወሳል። ከሳምንት በፊት በዝናብ የተነሳ ለመቋረጥ የተገደደው ጨዋታ ከትናንት በስቲያ አመሻሹን መደረግ የቻለ ሲሆን በሜዳ ላይም በውዝግቦች የታጀበ ክስተትን እያስመለከተን ቀጥሎ ኢትዮ ኤሌክትሪክ 2ለ0 እየመራ ባለበት ወቅት 87ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታው እንደደረሰ በስታዲየሙ ውስጥ ፓውዛውን የሚያበራው ሰራተኛ ባለመኖሩ የተነሳ ጨዋታው ትናንት ረፋድ ቀሪ ደቂቃዎች ከተደረጉበት በኋላ በመጨረሻም ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታውን 2ለ0 አጠናቋል።

ከትናንት በስቲያ በመጀመሪያው አጋማሽ ጭማሪ ደቂቃ ላይ አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለን በቀይ ካርድ ያጡት ድሬዳዋዎች በዕለቱ ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ላይ ቅሬታን ያቀረቡ ሲሆን በክለባችንም ላይ ግልፅ የውጤት ማስቀየር የዳኝነት በደል አድርሶብናል ይጣራልን በማለት ስድስት አንቀፆችን በመጥቀስ ለኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ፣ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና ለብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ደብዳቤን ስለማስገባቱ ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ የደረሳት መረጃ አመላክቷል።

ቡድኑ በደብዳቤው እንዳለው ከሆነ “በፍፁም ቅጣት ምት መምቻ አካባቢ የተጋጣሚ ተጫዋቾች በግልጽ በሚታይ መልኩ አስመስለው እየወደቁ ተደጋጋሚ ቅጣት ምቶች ተሰጥቶብናል ፣ የተጋጣሚ ተጫዋች ሆን ብሎ ወድቆ የፍፁም ቅጣት ምት ተሰጥቶብናል ይህም የተጋጣሚ ቡድንን ለማገዝ ሆን ተብሎ የተደረገ ስለመሆኑ ፣ ከጨዋታው መጀመር አንስቶ አላስፈላጊ ቃላቶችን ዳኛው ቴዎድሮስ ምትኩ በመጠቀም ተጫዋቾችን ሲያስፈራራ እንደነበር እና አላስፈላጊ ካርዶችን በመስጠት በኋላም አሰልጣኝ ይታገሱን በቀይ ማሰናበቱ ፣ በመልበሻ ቤት አካባቢ የግብ ጠባቂ አሰልጣኛችንን በኳስ ወርውሮ ተማቷል እና በመጨረሻም ስታዲየሙ መብራት ሳይኖረው ከሌሎች ዳኞች ጨዋታውን እንዲያቋርጠው ቢነገረውም ሆን ብሎ ጨዋታውን አካሂዷል” እና መሰል ዝርዝር ጉዳዮችን በመጥቀስ ነው ክለቡ ቅሬታውን ያቀረበው።