ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ስሑል ሽረ ከ ወላይታ ድቻ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ስሑል ሽረ ከ ወላይታ ድቻ

ወላይታ ድቻ የአሸናፊነት መንፈሱን መልሶ ለማግኘት ስሑል ሽረ ደግሞ በሊጉ የመቆየት ተስፋውን ለማለምለም የሚያደርጉት ጨዋታ የ27ኛው ሳምንት ቀዳሚ መርሐግብር ነው።

በአስራ ስምንት ነጥቦች 17ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ስሑል ሽረዎች የ2ኛውን ዙር ዐይን ገላጭ ድል ፍለጋ የጦና ንቦቹን ይገጥማሉ።

በ19ኛው ሳምንት ወልዋሎን አንድ ለባዶ ካሸነፈ ወዲህ በተከናወኑ ሰባት ጨዋታዎች ድል ማድረግ ያልቻለው ስሑል ሽረ አሁንም አካሄዱን ማስተካከል አልቻለም። በ2ኛው ዙር ሙሉ ነጥብ ማሳካት ያልቻለው ቡድኑ ከውድድር ዓመቱ አጋማሽ መጀመር በኋላ በተከናወኑ 7 መርሐግብሮች ማግኘት ከሚገባው 21 ነጥብ 3 ብቻ ማሳካቱን ተከትሎ በወራጅ ቀጠናው ለመቆየት ተገዷል። የነገውን ጨምሮ ቀጣይ ጨዋታዎች ላይ የሚያገኛቸው ነጥቦችም ከበላዩ ካሉት ክለቦች ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ እጅግ ወሳኝ ይሆናሉ።

ስሑል ሽረ አንድ ነጥብ ብቻ ካገኘባቸው አምስት መርሐግብሮች አገግሞ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቶ መውጣት ቢችልም አሁንም ዘርፈ ብዙ ችግሮች ያሉበት ቡድን ነው። የአሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት ቡድን በቀላል ስህተቶች ግብ የሚያስተናግድበትን አኳኋን በውስን መልኩ በመቅረፍ ባለፉት 12 መርሐግብሮች በጨዋታ ከ 1 ግብ በላይ ባያስተናግድም በማጥቃት ረገድ ያለው ውጤታማነት ግን እጅግ ዝቅተኛ ነው። ቡድኑ በ2ኛው ዙር በተከናወኑ 7 ጨዋታዎች 1 ግብ ብቻ ማስቆጠሩም የድክመቱ ማሳያ ነው። ቡድኑ ተፈላጊውን ውጤት ለማግኘትም የማጥቃት አጨዋወቱን ጥራት ከፍ ማድረግ በእጅጉ ያስፈልገዋል።

በ37 ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወላይታ ድቻዎች ከሰንጠረዡ ወገብ ላለመንሸራተት ወደ ድል መንገድ መመለስ ይኖርባቸዋል።

በመደዳ አራት ጨዋታዎች ላይ ድል አድርገው በ2ኛው ዙር መልካም አጀማመር በማድረግ ከመሪዎቹ ጎራ የነበሩት የጦና ንቦቹ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ከደረሰባቸው ሽንፈት በኋላ ወደ ሰንጠረዡ አጋማሽ ተንሸራተዋል። በወራጅ ቀጠናው ከሚገኘው ስሑል ሽረ የሚያደርጉት የነገ ጨዋታ በማሸነፍም ደረጃቸውን የሚያሻሽሉበት ዕድል ለማግኘት እንደሚጥሩ ይጠበቃል።

በማራኪ እንቅስቃሴ እና በርከት ባሉ የግብ ሙከራዎች ታጅቦ በተካሄደው ጨዋታ በሀድያ ሆሳዕና የሦስት ለአንድ ሽንፈት የደረሰባቸው ወላይታ ድቻዎች በጨዋታው መልካም አጀማመር ማድረግ ቢችሉም በተቀሩት ደቂቃዎች ግን በተጋጣሚያቸው ብልጫ ተወስዶባቸው ለመሸነፍ ተገደዋል። በጨዋታው ከወትሮው በተለየ አፍሳሽ እንዲሁም ለተጋጣሚ ፈጣን ሽግግሮች ተጋላጭ የነበረው የመከላከል አደረጃጀትም በነገው ዕለት መሻሻል የሚገባው ድክመት ነው። የጦና ንቦቹ በነገው ዕለት በሰባት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረ ቡድን እንደመግጠማቸው ከበድ ያለ ፈተና ይጠብቃቸዋል ተብሎ ባይገመትም በአምስት መርሐ-ግብሮች መረቡን አስከብሮ ከወጣ በኋላ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አራት ግቦች ያስተናገደው የኋላ ክፍላቸው ግን ወደ ቀድሞ ጥንካሬው መመለስ ይኖርበታል። በተለይም በመጨረሻው ጨዋታ የተስተዋሉ ግለ-ሰባዊ እና መዋቅራዊ የመከላከል ስህተቶች ካሁኑ መታረም ይገባቸዋል።

በስሑል ሽረ በኩል አምበሉ ነፃነት ገብረመድኅን በቅጣት ምክንያት አይሰለፍም፤ በጦና ንቦቹ በኩል ተከላካዩ አዛርያስ አቤል በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ መሆኑ ሲታወቅ መጠነኛ ጉዳት ያለበት የገጠመው የቀኝ መስመር ተከላካዩ ኬኔዲ ከበደም ለነገው ጨዋታ የመድረሱ ነገር አጠራጣሪ ነው። የተቀሩት የቡድኑ አባላት ግን ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ሆነው እንደሚቀርቡ ይጠበቃል።

የተሰረዘው እና በስሑል ሽረ የሁለት ለባዶ አሸናፊነት የተጠናቀቀውን የ2012 ጨዋታ ሳይጨምር 3 ጊዜ የተገናኙት ክለቦቹ በሁለቱም ጨዋታዎች አቻ ሲለያዩ ወላይታ ድቻ 1 ጊዜ አሸንፏል።  በጨዋታዎች ወላይታ ድቻ 2 ስሑል ሽረ ደግሞ   1 ግብ አስቆጥረዋል።