በወራጅ ቀጠናው የሚገኙ ክለቦችን የሚያገናኘው ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች እነሆ!
በሃያ አንድ ነጥቦች 16ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አዳማ ከተማዎች ከስድስት ድል አልባ የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ በሊጉ ግርጌ የተቀመጠውን ወልዋሎ ይገጥማሉ።
በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ተከታታይ ሽንፈት የቀመሱት አዳማዎች በ15ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው ሀዋሳ ከተማ ያላቸው የነጥብ ልዩነት ስድስት ደርሷል፤ ይህንን ተከትሎ ለከርሞ በሊጉ ለመቆየት በአንፃራዊነት ቀለል ያለ ፉክክር ይገጥማቸዋል ተብሎ ከሚገመተው የነገ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማግኘት በእጅጉ ያስፈልጋቸዋል። ይህ እንዲሳካ ግን ዘርፈ ብዙ መሻሻሎች ከቡድኑ ይጠበቃል፤ ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች አስራ አንድ ግቦች ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀትም አንገብጋቢ መፍትሔ የሚሻ የቡድኑ ድክመት ነው።
ካለፉት ስድስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው አስራ ስምንት ነጥብ ሁለቱን ብቻ ያሳካው ቡድኑ በመከላከል አደረጃጀቱ ከሚጠበቀው ለውጥ በተጨማሪ በተጠቀሱት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ብቻ ማስቆጠር የቻለው የማጥቃት አጨዋወቱንም ማሻሻል ግድ ይለዋል።
በአስራ አንድ ነጥቦች 18ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወልዋሎዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ በሊጉ የመቆየታቸው ጉዳይ አጣብቂኝ ውስጥ እየገባ እዚህ ደርሰዋል። የውድድር ዓመቱ ለማትረፍ ያላቸው እንጥፍጣፊ ዕድል ለመጠቀምም በነገው ዕለት በወራጅ ቀጠናው የሚገኝውን አዳማ ከተማ ይገጥማሉ።
በውድድር ዓመቱ በአንድ አጋጣሚ ብቻ ድል ያደረጉት እና ሙሉ ነጥብ ካገኙ አስር ጨዋታዎች ያለፋቸው ወልዋሎዎች በዚህ አካሄድ በሊጉ የመቆየት ዕድላቸው ጠባብ ቢሆንም ብያንስ
በወራጅ ቀጠናው ካሉ ሌሎች ክለቦች ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት በማጥበብ ላለመውረድ የሚደረገውን ፉክክር ለመቀላቀል ከእያንዳንዱ ጨዋታ ነጥብ ይዘው መውጣት ይኖርባቸዋል።
በ17ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ስሑል ሽረ በሰባት ነጥብ ከነገው ተጋጣሚው አዳማ ከተማ ደግሞ በአስር ነጥቦች ርቀት ላይ የሚገኘው ቡድኑ በቅርብ ሳምንታት በማጥቃቱ በኩል ውስን መሻሻሎች ማሳየት ቢችልም የኋላ ክፍሉ በአፍሳሽነቱ ቀጥሏል።
የፊት መስመሩ በአራት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ካስቆጠረባቸው ሳምንታት በኋላ በተከናወኑ አራት መርሐ-ግብሮች አራት ግቦች ማስቆጠር ቢችልም በተጠቀሱት ጨዋታዎች ያስተናገዳቸው ግቦች ሰባት ናቸው። በቀጣይም የመከላከል ድክመቱን ማሻሻል ከቡድኑ ይጠበቃል።
በአዳማ ከተማ በኩል መጠነኛ ጉዳት የገጠመው ቢኒያም ዐይተን የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ነው፤ ሌሎቹ የቡድን አባላት ግን ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው። ወልዋሎዎች በቅጣትም ሆነ በጉዳት የሚያጡት ተጫዋች የለም።
በ2012 የተሰረዘውን የውድድር ዘመን ሳይጨምር ሁለቱ ቡድኖች 5 ጊዜ ተገናኝተው አዳማ 3 ሲያሸንፍ፣ ወልዋሎ አንድ አሸንፎ ቀሪዋን አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይለዋል። አዳማ 8፣ ወልዋሎ 2 አስቆጥረዋል።