ቅዱስ ጊዮርጊስ ኬንያዊ አጥቂ ላይ አነጣጥሯል

የአምናው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ ኬኒያዊው የተስካር ኤፍ.ሲ. አጥቂ ጄስ ጃክሰን ዌር ላይ ትኩረት ማድረጉን ከኬንያ የሚወጡ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ የ26 ዓመቱ አጥቂ ጄስ በቅዱስ ጊዮርጊስ ለ3 ቀናት የቆየ የሙከራ ጊዜ ያሳለፈ ሲሆን ከታህሳስ 2 እስከ 4 በአዲስ አበባ መቆየቱ ታውቋል፡፡

ጄስ በተለያዩ ምስራቅ አፍሪካ ክለቦች የሚፈለግ ሲሆን ከአንድ የቱኒዚያ ክለብ ጋር ስሙ ተያይዟል፡፡ ፈረሰኞቹ ያለባቸውን የአጥቂ ችግር ለመፍታት ተጫዋቾችን ማሰስ ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል፡፡ እንደ kplchat.com ዘገባ ከሆነ ፈረሰኞቹ በጄስ የሙከራ ጊዜያት ተደንቀዋል፡፡ ጄስ ስለቆይታው “የቴክኒክ ኃላፊዎቹ ባለኝ ችሎታ ተደንቀዋል፡፡ በወሩ መጨረሻ እንደሚያገኙኝ ነግረውኛል፡፡ ለወደፊት ጥሩ ነገር እንደሚመጣ ተስፋ አደርጋለው፡፡” ሲል ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርገው ጉዞ መስመር እየያዘ እንደሆነ ጠቁሟል፡፡ ከተስካር በፊት ለማታህር ዩናይትድ የተጫወተው ጄስ በውድድር ዘመኑ ለኬንያው ተስካር 9 ጎሎችን አስቆጥሯል፡፡ የክለቡም ኮኮብ ግብ አስቆጣሪ ነበር፡፡ በቅርብ ጊዜያት ባሳየው አቋምም ለኬንያ ብሄራዊ ቡድን ተመርጧል፡፡

ያጋሩ