“ጊዜው የረፈደብን ይመስላል፡፡ ያም ቢሆን የመቆየት ተስፋ አለን” ጥላሁን መንገሻ

በዘንድሮው የውድድር ዘመን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደገው ሀዲያ ሆሳዕና ሊጉ የተራራ ያህል የገዘፈበት ይመስላል፡፡ ከ19 ጨዋታ 1 ድል እና 7 ነጥብ ብቻ አስመዝግቦም በሊጉ ግርጌ ተቀምጧል፡፡

በፕሪሚየር ሊጉ ታሪክ ደካማ የውድድር ዘመን እያሳለፉ ከሚገኙ ክለቦች አንዱ የሆነው ሀዲያ ሆሳዕና በሁለተኛው ዙር ከግማሽ ደርዘን በላይ አዳዲስ ተጫዋቾችን ቢያስፈርምም የውጤት ማጣቱ ተባብስ ቀጥሏል፡፡

በሁለተኛው ዙር ክለቡን ከመውረድ ለማትረፍ ሃሃፊነት የተረከቡት አሰልጣኝ ጥላሁን መንገሻ በውድድር አመቱ መጀመርያ የተሰራው ስህተት አሁን ላሉበት ደረጃ አስተዋፅኦ ማድረጉን ከትላንትናው የጊዮርጊስ ሽንፈት በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡

” ሀዲያ ሆሳዕና በፕሪሚየር ሊጉ ላይ ብዙ ልምድ የሌለው ቡድን ነው ። በአመቱ መጀመርያም ስህተቶች ተሰርተዋል፡፡ ምክንያቱም የፕሪሚየር ሊግ ልምድ ያላቸው ተጨዋቾች አልያዘም ። እነዛ ችግሮች ሲንከባለሉ መጥተው ሁለተኛው ዙር መጥተዋል፡፡ ”

ይላሉ፡፡

” በሁለተኛው ዙር የተጫዋች ምልመላው ከተጠናቀቀ በኋላ ነው የተቀጠርኩት፡፡ ስለዚህ ባሉት ተጨዋቾች ነው እየሰራን ያለነው፡፡ እንደዛም ሆኖ ግን በተለያዩ ክለቦች ልምድ ያላቸው እንደነ መስቀሌ አይነት ተጨዋቾች ለማምጣት ተሞክሯል፡፡ እነሱም በደረሰባቸው ጉዳት በተከታታይ ጨዋታ ማድረግ አልቻሉም ። በፕሪሚየር ሊጉ ውስጥ ለመቆየት ክለቡ አመራሩ ያደረጉት ጥረት ጥሩ ነው ። ግን  ጥራት ባለው ተጨዋችና ልምድ ባላቸው ተጨዋቾች ያልታገዘ በመሆኑ ይህ ሽንፈት እየቀጠለ ሄዷል፡፡ “

ሲሉም ያክላሉ፡፡

የሀዲያ የውድድር ዘመኑ ሁኔታ በእርግጥም አሰልጣኝ ጥላሁን ያነሱት ሀሳብ ይገልፀዋል፡፡ በእንቅስቃሴ ከሌሎቹ የጎላ ልዩነት ባይኖራቸውም ግብ ለማስቆጠር እና ድል ለማድረግ የስብስብ ጥራት ይጎድላቸዋል፡፡ አሁን ይህን መስመር ለማስያዝ እየጣሩ ቢሆንም ጊዜው እየረፈደባቸው እንደሆነም አልሸሸጉም፡፡

” አዎ፡፡ በእንቅስቃሴ ብዙም አንበለጥም፡፡ ነገር ግን ሽኝፈቶች ሲደጋገሙ ፍራስትሬሽን ይበዛሉ፡፡ በአብዛኛው ራሳችን ላይ ጎል እንዳይቆጠርብን ቅድሚያ በመስጠት ጎል ለማግባት ነው የምንጫወተው ። ነገር ግን ላለመውረድ የሚጫወት ቡድን ጎል እንዳይቆጠርበት ጥንቃቄ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ጎል ማስቆጠር አለበት። ጎል ማስቆጠሩ ላይ ባለው ሂደት ያገኘናቸው ተጨዋቾች (እነ አሸናፊ አደም) ገና ለመጀመርያ ጊዜ መሰለፉ ነው፡፡ ፐርፎርማሱም አልመጣለትም ነበር፡፡ አሁን እያስተካከልን እየሄድን ነው፡፡ ነገር ግን ጊዜው የረፈደብን ይመስላል።”

በመጨረሻም በሊጉ ለመቆየት ያላቸውን ጭላንጭል ተስፋ መጠቀም እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

” በፕሪሚየር ሊጉ ለመቆየት እድሎችን በሙሉ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ አሁን ላይ እድሎችን ለመጠቀም ቀሪ ጨዋታዎች ላይ ጠንክሮ መጫወት ያስፈልጋል፡፡ እድሎች እያሉ ካልተጠቀምንበት ከባድ ነው ። ያም ቢሆን አሁንም ለመቆየት ተስፋ አለን፡፡ ወርደናል ብዬ አላስብም። “

Leave a Reply