“በኢኤንፒፒአይ ክለብ የውስጥ ችግር አለ” ኡመድ ኡኩሪ

ኢትዮጵያዊው አጥቂ ኡመድ ኡኩሪ በ2007 በግብፅ ፕሪምየርሊግ ለሚወዳደረው ኢኤንፒፒአይ ክለብ የአራት ዓመት ውል ከፈረመ ወዲህ በፔትሮሊየም አምራቾቹ ክለብ ህይወት ቀላል የሆነለት አይመስልም፡፡

ኡመድ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት የኢኤንፒፒአይ የውስጥ ችግር ክለቡን እየጎዳው ነው ይላል፡፡ “ክለቡ ውስጣዊ ችግር አለበት፡፡ ኢኤንፒፒአይ ከአል አሃሊ እና ዛማሌክ ቀጥሎ በግብፅ ትልቁ ክለብ ነው፡፡ ነገር ግን ጠንካራ አሰልጣኝ ስለሌለው ቋሚ አሰላለፍ እንኳን የሚመርጡት ተጫዋቾች ናቸው፡፡ መልበሻ ክፍሉ በቡድኖች የተከፈለ ነው፡፡ መልበሻ ክፍሉ ውስጥ አንድ ቡድን አለ፡፡ ከዚህ ቡድን አባላት ጋር ወዳጅነት ከፈጠርክ ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ የመግባት እድልህ ከፍ ይላል፡፡ የዚህ ቡድን አባላት በተለይ አቋማቸው ወርዶ እንኳ ቋሚ ናቸው፡፡ በክለቡ ውስጥ ሶስት የውጪ ሃገር ተጫዋቾች አለን፡፡ ነገር ግን ክለቡ እኛን አንድ ላይ አጫውቶን አያውቅም፡፡” ይላል፡፡

በገንዘብ አቅሙ በግብፅ ውስጥ ከፍ ያለ ቦታ ከሚጣቸው ክለቦች መካከል የሆነው ኢኤንፒፒአይ በዘንድሮ አመት ሶስት ጊዜ የአሰልጣኝ ለውጥ አድርጓል፡፡ የቀድሞ የአሃሊ ኮከብ ሃኒ ራምዚ በገዛ ፍቃዱ ክለቡን ሲለቅ ሃማዳ ሰድኪ ደግሞ ከስራ ገበታቸው ከተሰናበቱ በኋላ የቀድሞ የዳክልያ ክለብ አሰልጣኝ የነበረውን አላ አብደል አልን አሰልጣኝ አድርጎ ቀጥሯል፡፡

በሁሉም አሰልጣኞች የመሰለፍ እድል የተነፈገው ኡመድ ክለቡን ያሰለጠኑት አሰልጣኞች ለምን ከቋሚ አሰላለፍ ውጪ አንዳደረጉት ያስረዳል፡፡ “በውድድር አመቱ የመጀመሪያ አምስት የሊግ ጨዋታዎች የዝውውር ጉዳዬ ባለመጠናቀቁ ሳልሰለፍ ቀርቻለው፡፡ የዝውውር ጉዳዬ ከተጠናቀቀ በኃላ ከአሰልጣኝ ሃኒ ጋር ተነጋግሬ ነበር፡፡ እሱ እኔን በመስመር ላይ ነበር ሊያሰልፈኝ ያሰበው፡፡ እኔ ደግሞ ስኬታማ እንቅስቃሴ የማደርገው አጥቂ ሆኜ ስሰለፍ ነው፡፡ ከአሰልጣኝ ሃኒ ጋር በዚህ ጉዳይ ተስማምተን ነበር፡፡ በመሃል የአሰልጣኝ ለውጥ ተደርጎ ሰድኪ ሲመጣ ቋሚ ሊያደርገኝ አልፈለገም፡፡ ክለቡ የአጥቂ ችግር ስለነበረበት እኔን ለማስፈረም ብዙ ደክሟል፡፡ ለቀድሞ ክለቤ ኢቲሃድ አሌክስአንደሪያ ገንዘብ ክፍሎ ነበር ያሰፈረመኝ፡፡ ሰዲኪ ሶሞሃ እያለ አንድ ከተማ ስለነበርን ስለእኔ በደንብ ያውቅ ነበር፡፡ ነገር ግን ሊያሰልፈኝ አልፈለገም፡፡” ሲል ሃሳቡን ያብራራል፡፡

13233245_824180117713158_1778958702_n

የ2006 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ተጫዋች እና ግብ አግቢው ኡመድ በካፍ ኮንፌድሬሽን ካፕ አንደኛ ዙር ኢኤንፒፒአይ የኮትዲቯሩን አፍሪካ ስፖርትስ 4-1 ሲያሸንፍ አንድ ግብ ሲያስቆጥር ለመጀመሪያው ግብ መገኘትም ቁልፍ ሚና ተጫውቷል፡፡ በተመሳሳይ ውድድር ከጋቦኑ ሲኤፍ ሞናና ጋር ሊበርቪል ላይ ለ20 ደቂቃዎች ከተጫወተ በኃላ በሊጉ ከአሃሊ ጋር በተደረገውም ጨዋታ ተቀይሮ ገብቶ መልካም እንቅስቃሴ ማሳየት ችሏል፡፡ ከአሃሊው ጨዋታ በኃላ ግን ኡመድን በኢኤንፒፒአይ መለያ ልንመለከተው አልቻልንም፡፡

“በአሃሊ ከተሸነፍንበት ጨዋታ በኃላ ለሞናና የመልስ ጨዋታ ተዘጋጅቼ ነበር፡፡ ቢሆንም ለጨዋታው ሆቴል ልንገባ አከባቢ ታመምኩ፡፡ ህመሜ ከባድ ስለነበር በሞናናው የመልስ ጨዋታ ሳልሰለፍ ቀረው፡፡ ከህመሜ ካገገምኩኝ በኃላ አዲሱ አሰልጣኝ (አላ አብደል አል) በተደጋጋሚ ከቡድኑ ውጪ አድርጓኛል፡፡ ባለፈው ሳምንት በወዳጅነት ጨዋታ ሁለት ግብ አስቆጥሬ አንድ ግብ የሆነ ኳስ አቀብዩ ነበር፡፡ ከጨዋታው በኃላ ስለእኔ ከሚዲያዎች አሰልጣኙ ሲጠየቅ ኡመድ ጥሩ እና ምርጥ ተጫዋች ነው ብሎ ነበር፡፡ የሚገርመው በሊግ ጨዋታ ከኢስማኤሊ ጋር ስንጫወት ከቡድኑ ውጪ አደረገኝ፡፡ በግብፅ ዋንጫ ላለብን ጨዋታም እንዲሁ ከቡድኑ ውጪ ተደርጊያው፡፡” (ኢኤንፒፒአይ በግብፅ ዋንጫ ሩብ ፍፃሜ ከኤል ሜሪክ ስፖርት ክለብ ጋር ይጫወታል)

ኢኤንፒፒአይ ያለው ስብስብ ሁለት ቡድን ይሰራል የሚለው ኡመድ ከወዲሁ የመውጫውን በር መፈለጉን አልሸሸገም፡፡

“በተጠባባቂ ወንበር ላይ ያሉት ተጫዋቾች አማካይ እና ተከላካይ ብቻ ሆነው አንድን አጥቂ ከቡድን ውጪ ማድረግ በጣም የተሳሳተ አሰራር ነው፡፡ ክለቡን ለመልቀቅ አስቤያለው፡፡ ይህንን ሃሳቤን ወኪሌ ያውቃል፡፡ ሰኔ መጨረሻ ላይ ከውድድር ዘመኑ ማብቂያ በኃላ ከወኪሌ ጋር በመሆን ከክለቡ ጋር ያለኝን ቀሪ የሶስት ዓመት ውሌን በስምምነት የማፈርስበትን መንገድ እፈልጋለው፡፡ እኔ መጫወት እፈልጋለው፡፡ ቀሪ የውል ዘመኔን እንደዚህ ባለ መልኩ ማሳለፍ አልፈልግም፡፡” ሲል ሃሳቡን አጠናቅቋል፡፡

Leave a Reply