ኮንፌድሬሽን ካፕ፡ ወደ ምድብ ያለፉ 8 ክለቦች ታውቀዋል

የ2016 ኦሬንጅ ኮንፌድሬሽን ካፕ የምድብ አላፊዎች ትላንት በተለያዩ የአፍሪካ ከተሞች በተደረጉ ጨዋታዎች ታውቀዋል፡፡ ምስራቅ አፍሪካ ከወዲሁ አንድ ተወካይ ስታረጋግጥ የሰሜን አፍሪካ የበላይነት አሁንም በውድድሩ ላይ ተንፀባርቋል፡፡

ሊበርቪል ላይ ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል የመሃል ዳኛ ባምላክ ተሰማ በመራው ጨዋታ የጋቦኑ ሲኤፍ ሞናና የቱኒዚያው ኤቷል ደ ሳህልን 1-0 መርታት ቢችልም ወደ ምድብ ለማለፍ ግን አልቻለም፡፡ ሶስ ላይ ኤቷል 2-0 ያሸነፈ በመሆኑ ወደ ምድብ ለመግባት አልተቸገረም፡፡ ለሞናና የአሸናፊነቷን ግብ ሉዊ ኦንቻንጋ ከመረብ አሳርፏል፡፡
የታንዛኒያው ያንግ አፍሪካንስ በአንጎላው ሳግራዳ ኤስፔራንሳ ቢሸነፍም ወደ ምድብ ማለፍ ችሏል፡፡ ሳግራዳ በላቭ ካቡንጉላ ግብ 1-0 ቢያሸንፍም ከሁለት ሳምንት በፊት ዳሬ ሰላም ላይ 2-0 በመረታቱ ወደ ምድብ የሚያሳልውን ውጤት ማግኘት አልቻለም፡፡ ውጤቱ ያንጋ ወደ ምድብ ያለው ብቸኛው የምስራቅ አፍሪካ ቡድን ያደርገዋል፡፡
ሌላው የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ የሱዳኑ ኤል ሜሪክ ማራካሽ ላይ በካውካብ ማራካሽ 2-0 ተሸንፎ ከውድድር ውጪ ሆኗል፡፡ ለማራካሹ ክለብ አል ፋኪህ ሁለቱንም ግቦች ማስቆጠር ችሏል፡፡ አምና በቻምፒየንስ ሊጉ ግማሽ ፍፃሜ ሁለት ክለቦችን ማሳተፍ የቻለችው ሱዳን ዘንድሮ በአፍሪካ መድረክ ተወካይ የላትም፡፡

ደቡብ አፍሪካ ላይ ጨዋታውን ሊጠናቀቅ በተቃረበበት ወቅት ሶስት ግብ አስተናግዶ የተመለሰው የጋናው ሚዲአማ በሜዳው እና ደጋፊ ፊት ማሜሎዲ ሰንዳውንስ 2-0 በማሸነፍ ወደ ምድብ መግባቱን አረጋግጧል፡፡ ለሚዲአማ የድል ግቦቹን ማሊክ አኮዋ በፍፁም ቅጣት ምት እና በርናድ ኦፎሪ አስገኝተዋል፡፡ አንድ የጋና ክለብ በንፌድሬሽን ካፑ ወደ ምድብ ሲገባ ይህ ከስምንት አመት በኃላ ለመጀመሪያ ግዜ ነው፡፡
የሞሮኮው ፉስ ራባት ወደ ምድብ በመግባት መልካም የሆነ ሳምንትን አሳልፏል፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ በሞሮኮ ቦቶላ ሊግ ዋይዳድ ካዛብላንካን ከሜዳው ውጪ 1-0 ያሸነው የመዲናዋ ክለብ የማሊውን ስታደ ማሊያንን 4-0 በሆነ ሰፊ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡ ለራባቱ ክለብ የድል ግቦቹን ሙስጠፋ ኮንዴ፣ መሃመድ ናሂሪ፣ የሱፍ ኒጄ እና ሙራድ ባትና ከመረብ አዋህደዋል፡፡
የግብፁ ምስር አል ማቃሳ ከአል አሃሊ ትሪፖሊ ፋዩም ላይ 1-1 በመለያየቱ ከኮንፌድሬሽን ካፑ ተሰናብቷል፡፡ ለመጀመሪያ ግዜ በውድድሩ ላይ የተካፈለው ማቃሳ በጋናዊው አጥቂ ናና ፖኩ ግብ መምራት ቢችልም የሊቢያውን ክለብ አድል በፍፁም ቅጣት ምት አቻ ማድረግ ችሏል፡፡ ሊቢያ ውስጥ ባለው ያለመረጋጋት ጨዋታዎቹን በገለልተኛ ሜዳ ሲያካሂድ የነበረው አሃሊ ትሪፖሊ በስተመጨረሻም ወደ ምድብ ማለፍ ችሏል፡፡
የቻምፒየንስ ሊጉ እና የኮንፌድሬሽን ካፑ የምድብ ድልድል ግብፅ ካይሮ በሚገኘው የካፍ ዋና ፅህፈት ቤት ማክሰኞ ግንቦት 16 ይካሄዳል፡፡

የዕረቡ ውጤቶች

ሲኤፍ ሞናና (ጋቦን) 1-0 ኤቷል ስፖርቲቭ ደ ሳህል (ቱኒዚያ) [1-2]
ሚዲአማ (ጋና) 2-0 ማሜሎዲ ሰንዳውንስ (ደቡብ አፍሪካ) [3-3]
ሳግራዳ ኤስፔራንሳ (አንጎላ) 1-0 ያንግ አፍሪካንስ (ታንዛኒያ) [1-2]
ፋት ዩኒየን ስፖርት ራባት (ሞሮኮ) 4-0 ስታደ ማሊያ (ማሊ) [4-0]
ካውካብ አትሌቲክ ክለብ ማራካሽ (ሞሮኮ) 2-0 ኤል ሜሪክ (ሱዳን) [2-1]
ምስር አል ማቃሳ (ግብፅ) 1-1 አል አሃሊ ትሪፖሊ (ሊቢያ) [1-1]

ወደ ምድብ የገቡ ክለቦች

ቲፒ ማዜምቤ (ዲ.ሪ. ኮንጎ)፣ ሞሊዲያ ኦሎምፒክ ቤጃያ (አልጄሪያ)፣ ኤቷል ደ ሳህል (ቱኒዚያ)፣ ሚዲአማ (ጋና)፣ ያንግ አፍሪካንስ (ታንዛኒያ)፣ ፉስ ራባት (ሞሮኮ)፣ አል አሃሊ ትሪፖሊ (ሊቢያ)፣ ካውካብ ማራካሽ (ሞሮኮ)

Leave a Reply