የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ከጋና ጋር በመጪው ዕሁድ አዲስ አበባ ላይ ጨዋታው ያደርጋል፡፡ ዛምቢያ ለምታዘጋጀው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በሚደረገው ጨዋታ ዙሪያ የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ግርማ 11ሃብተዮሃንስ ለሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርጋለች፡፡
ስለዝግጅት
ዝግጅታችን ባለፈው ከሶማልያ ጨዋታ በኃላ በነበረን አቋም ላይ የተሻለ ነገር ጨምረን ለመስራት፤ የተወሰኑ ተጫዋቾችንም አንደገና በመጨመር እና አቋማቸውን ለማጠናከር የሚያስችልንን ቅንጅት ለመስራት ሞክራናል፡፡
በመጀመርያው ጨዋታ የነበረውን የአጨራረስ ችግር ስለመቅረፍ
የአጨራረስ ችግር አሁንም አለብን፡፡ ነገርግን በተለያየ ምክንያት የተጫዋቾች ጉድለት ስለነበረብን ያንን የተጫዋቾች ጉድለት ለማሟላት እንደገና የማደራጀት እና አዳዲስ ተጫዋቾችም የመጨመር ስራ ስለነበረ እንደመጀመሪያው አይነት ነው ስራዎችን የሰራነው፡፡ ዞሮ ዞሮ በቀድሞውም ሆነ በአሁኑ የአጨራረስ ልምምዶችን ሰርተናል፡፡ በቲዮሪ ደረጃም ተነጋግረናል፡፡ ልጆቹም በክለብ ደረጃ ያላቸው ልምምድ ስላለ ያንን ተጠቅመው ውጤት ለማምጣት የምንችልበትን እንቅስቃሴ ያደረግነው፡፡
የስብስብ ወጥነት ችግር
ተጫዋቾችን ለመቀያየር ያስገደዱን ምክንያቶች አሉ፡፡ በህመም፣ የችሎታ ጉዳይ እና በMRI ምክንያት የወጡ ልጆች አሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች የግድ ተጫዋቾችን ለመቀነስ አስገድዶናል፡፡ ችግር እንደሚፈጥር ይታወቃል ፤ ነገርግን ከዚህ ውጪ መስራት አይቻልም፡፡ ያለው አማራጭ ይህ ብቻ ስለሆነ ነው፡፡
ስለ ጋና
የጋናን 2015/16 ኒውዚላንድ ላይ ያደረጉትን ጨዋታ በምስል ተመልክተናል፡፡ እያንዳንዱ ተጫዋች በቦታው ላይ በሚሰለፍበት ወቅት ሊያደርግ የሚገባውን ነገር በራሱ እንዲወስን እድል ተፈጥሯል፡፡ ጋና የራሱ ጥንካሬ ይኖረዋል፡፡ ልምዱ፣ ስሙ እና አቋሙም በአፍሪካችን ውስጥ የተሻለ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ እኛ ማድረግ የምንችለው የልጆቻችን አቅም ባገናዘበ መልኩ መስራት መቻል ነው፡፡ እያንዳንዱ ልጅ የአቅሙን ያህል መስራት ከቻለ በቃ ከዚያ በላይ የሚጠበቅብን ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ አቅማችንን አውቀን በአቅማችን የጋናን አጠቃቅ ስልት ተከላክለን እኛ ደግሞ አጥቅት መጫወት አለብን፡፡ እነሱ ልምድ አላቸው ረጅም ግዜ ስልጠናውን ወስደዋል ስም አላቸው፡፡ ይህ ግን በእኛ ላይ ተፅእኖ አያመጣም፡፡
ማሳካት የሚያልሙት ውጤት
በውድድር ሁልጌዜም የሚፈለገው ውጤት ማሸነፍ ነው፡፡ ምንም አይነት ቡድን ይሁን ሶማልያን ብንመለከተው ከእኛ ጋር የተጫወተው አሸንፋለው ብሎ ነው፡፡ ማንም ውድድር ውስጥ የሚገባው ለማሸነፍ ነው፡፡ አናሸንፍም የሚል አስተሳሰብ በውስጣችን የለም፡፡ ግባችን ማሸነፍ ነው፡፡ ነገር ግን ለማሸነፍ ስንሄድ ግን የሚመጡ ውጤቶችን በፀጋ እንቀበላለን፡፡ ምክንያቱም ዝግጅታችንን እናውቀዋለን ፤ አመጣጣችንን እናውቀዋለን፡፡ በጅምር ላይ ነው ያለነው፡፡ የህዝብ ድጋፍ ስላለን በተሻለ ሁኔታ ለመጫወት ዝግጁ ነን፡፡