የመውረድ ስጋት ውስጥ በመሆኑ አብዛኛው የ2015/16 የውድድር ዘመን ያሳለው የፕሪቶሪያው ክለብ ጎልደን አሮስን 2-1 ማሸነፍ ችሏል፡፡ የደቡብ አፍሪካ ፕሪምየር ሶከር ሊግ ዛሬ መቋጫውን ሲያገኝ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ፕሪቶሪያ በማሸነፍ አሁንም ላለምውረድ ተስፋውን አለምልሟል፡፡
በሜዳው ጎልደን አሮስን ያስተናገደው አማተክስ በቩዬሲሊ ንቶምባዬቴቲ በ28ኛው ደቂቃ ከጌታነህ ከበደ የተሻገረለትን ቅጣት ምት ተጠቅሞ መሪ ሲሆኑ ጌታነህ የመጀመሪያው ግማሽ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩት በቅጣት ምት የግብ ልዩነቱን ወደ ሁለት አስፍቷል፡፡ ሁለተኛው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት አማተክሱ ኔሙኮንደኒ በሁለተኛ ቢጪ ከሜዳ ሲወጣ አሮስን ከመሸነፍ ያለዳነች ግብ ግላድዊን ሺቶሎ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሯል፡፡
አማተክስ የውድድር ዓመቱን በ25 ነጥብ እና 17 የግብ ዕዳ በ15ኛነት የጨረሰ ሲሆን አስራ ስድስት ቡድኖች በሚካፈሉበት ሊግ ጆሞ ኮስሞስ መውረዱን አረጋግጧል፡፡ ማርቲዝበርግ ዩናይትድ ደግሞ በሊጉ መቆየቱን ያረጋገጠበትን ድል ዛሬ ማስመዝገብ ችሏል፡፡
በአብሳ ፕሪምየርሺፕ የሊግ መዋቅር መሰረት የናሽናል ፈርስት ዲቪዥን (የደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያ ዲቪዚዮን) ሻምፒዮን በቀጥታ ወደ አብሳ ፕሪምየርሺፕ ሲያድግ በውድድር ዓመቱ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሆነው የሚጠናቅቁት ቡድኖች በፕሪምየርሺፕ 15ኛ ሆኖ ከሚጨርሰው ክለብ ጋር በመጫወት አሸናፊው ወደ ሊጉ የሚያድግ ይሆናል፡፡ አማተክስ 15ኛ ሆኖ በመጨረሱ የዚህ ውድድር ተሳታፊ ሲሆን በውድድሩ ላይ ከዊትባንክ ስፐርስ እና ሃይላንድስ ፓርክ ጋር በሊጉ ለመቆየት ይፋጠጣል፡፡
የናሽናል ፈርስት ዲቪዥን ሻምፒዮኑ ባሮካ ከወዲሁ ወደ አብሳ ፕሪምየርሺፕ ማደጉን አረጋግጧል፡፡