የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ከጋና ጋር በአዲስ አበባ ስታዲየም ወደ አፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ለማለፍ የመጀመሪውን ጨዋታውን ያደርጋል፡፡ ቡድኑ ባረፈበት ኢትዮጵያ ሆቴል የተገኘችው ሶከር ኢትዮጵያ ከብሄራዊ ቡድኑ ግብ ጠባቂ ተክለማሪያም ሻንቆ፣ ከአምበሉ ዳንኤል ራህመቶ እና አጥቂው አሜ መሃመድ ጋር ስለጨዋታው እና መሰል ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ቆይታ አድርጋለች፡፡
“የትኛውንም ቡድን አግዝፈን የምናይበት መንገድ የለም” ዳንኤል ራህመቶ
“ዝግጅታችን ጥሩ ነበር፡፡ ጥሩ ዝግጅት እያደረግን ነው ያለነው፡፡ በአብዛኛው የቅንጅት ስራ ስንሰራ ነበር፡፡ የተጨመሩት ልጆች ከውድድር ላይ ስለመጡ እነሱ ላይ እየተሰራ ያለው የቅንጅት ስራ ነው፡፡”
“ስለጋና በአሰልጣኞቻችን በኩል የተነገረን ነገር አለ፡፡ ሲቀጥል ደግሞ የነሱን አንዳንድ ጨዋታዎችን በምስል መመልከት ችለናል፡፡ ቢሆንም በእኛ በኩል ተዘጋጅተናል፣ የትኛውንም ቡድን አግዝፈን የምናይበት መንገድ የለም፡፡ ነገር ግን በጥንቃቄ የተሻለ እንቅስቃሴ እናሳያለን ብለን እናስባለን፡፡”
“ከሶማልያው ጨዋታ የበለጠ ጫና ይኖርብናል የሚል ዕምነት የለኝም፡፡ ምክንያቱም አብዛኞቻችን ኢንተርናሽናል ጨዋታ ስናደርግ የመጀመሪያችን ነበር፡፡ ከዛ አንፃር ነው ብዙ ግብ ማስቆጠር ያልቻልነው፡፡ አሁን ብዙም ባይሆን ሁለት ኢንተርናሽናል ጨዋታ አድርገናል፡፡ በሁለቱ ጨዋታዎች ብዙ ነገሮችን ነው የተማርንበት፡፡”
“በሜዳችን እናሸንፋለን ብዬ አስባለው” አሜ መሃመድ
“ከተሰበሰብን ሁለት ሳምንት ይሆነናል፡፡ በዚሁ ግዜ ጥሩ ዝግጅት ለማድረግ ችለናል፡፡ በዚህ ጨዋታ ፈጣሪ ካለ ግብ የማስቆጥር ይመስለኛል፡፡ ጋና ጠንካራ ቡድን ነው፡፡ ሁሉም ቡድን ጠንክሮ ከሰራ ጠንካራ መሆን ይችላል፡፡ የነሱ ጥንካሬ እኛን አያስፈራንም፡፡ በሜዳችን እናሸንፋለን ብዬ አስባለው፡፡”
“በአቋም ምክንያት የተቀነሱ ተጫዋቾች አሉ፡፡ አዲስ የመጡት ደግሞ ከተቀነሱት የተሻለ ብቃት ያላቸው ናቸው፡፡ ከነሱ ጋር ለመግባባት የቅንጅት ስራ እየሰራን ነው፡፡ ጥሩ ቅንጅት መፍጠር ከቻልን ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ እንችላለን ብዬ አስባለው፡፡”
“ጋና ከሶማልያ የተሻለ ነው ብለን የምንፈራበት ምክንያት የለም” ተክለማሪያም ሻንቆ
“ከሶማልያ ጋር ባደረግነው ጨዋታ ብዙም አንድ ላይ አልነበርንም፡፡ ለመቀናጀትም የሳምንት ያህል ግዜ አልነበረንም፡፡ እንደ መጀመሪያ የኢንተርናሽናል ግጥሚያችን እና ህዝቡ ውጤቱን በመፈለጉ ጫና ውስጥ ገብተን ነበር፡፡ በመልሱ ጨዋታ ረጅም ግዜ በመዘጋጀታችን ጅቡቲ ላይ ከጥሩ ጨዋታ ጋር ማሸነፍ ችለናል፡፡ በርግጥ ጋና ከሶማልያ ይሻላል፡፡ ጋና ከሶማልያ የተሻለ ነው ብለን የምንፈራበት ምክንያት ግን የለም፡፡ አሰልጣኞቻችን የሰጡን ልምምድ እና ታክቲክን ተከትለን ሜዳ ላይ ከተገበርን ምንም የማናሸንፈበት ምክንያት የለም፡፡”
“የተወሰኑ የጨዋታ ምስሎችን አግኝተን ከዕረቡ ጀምሮ ለመገምገም ሞክረናል፡፡ ከረጅም ርቀት ወደ ግብ አክርረው መምታት ላይ ጥሩ ናቸው፡፡ በተመለከትነው ምስል መሰረት ልምምዶችን ሰርተናል፡፡ እኔም እንደግብ ጠባቂነቴ በረጅሙ የሚልኩትን ኳሶች ስላየው ጥንቃቄ ለማድረግ እሞክራለው፡፡”
“እኛ በሙሉ ልብ ተዘጋጅተናል፡፡ በእርግጠኝነት ህዝባችንም ይደግፈናል፡፡ ጥሩ ጨዋታ እና የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንጫወታለን፡፡”