ሪፖርት ፡ ኢትዮጵያ በመጀመርያ ጨዋታ ጋናን 2-1 አሸነፈች

በዛምቢያ አዘጋጅነት በሚደረገው የ2017ቱ የአፍሪካ ወጣቶች ዋንጫ ለመሳተፍ የማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ቡድን ዛሬ የጋና አቻውን በአዲስ አበባ ስታዲየም አስተናግዶ 2-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። በጨዋታው ድንቅ እንቅስቃሴ ያደረገው የጅማ አባቡናው አጥቂ አሜ መሐመድ የቡድኑን ሁለት የማሸነፊያ ግቦች ከመረብ አሳርፏል።

ጨዋታው በተጀመረ በ4ኛው ደቂቃ ሱራፌል አወል ከጋናው ተከላካይ ዳንኤል አሞሃ በመንጠቅ ወደግብ የሞከረው ኳስ በግብ ጠባቂው ክዋሜ ባህ ቢመለስም ኦሜ መሐመድ በቀላሉ የተመለሰውን ኳስ በማስቆጠር ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል። ግቡ የኢትዮጵያ ተጫዋቾችን የራስ መተማመን የጨመረ ሲሆን የጋና ተጫዋቾች ላይ የመደናገጥ ስሜት ፈጥሯል። በ9ነኛው ደቂቃም የጋናው አይዛኩ ኮንዳን ስህተት በመጠቀም ኦሜ መሐመድ ለራሱና ለቡድኑ ሁለተኛ ግብ አስቆጥሯል። በመጀመሪያው ግማሽ ቀሪ ደቂቃዎች የጋና ተጫዋቾች ኳስን ከመስመር በማሻማት እና ከረጅም ርቀት ወደጎል በመምታት ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም ግብጠባቂው ተክለማሪያም ሻንቆን የፈተነ ሙከራ ማድረግ ሳይቻላቸው ቀርቷል።

በሁለተኛው የጨዋታው አጋማሽ መጀመሪያ የጋናው አሠልጣኝ ዲዲ ድራማኒ የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ኢቫንስ ሜንሳህ እና ሞሰስ ሳርፖንግ ቀይረው ወደሜዳ በማስገባት ግብ የማግኘት ጥረታቸውን ሲቀጥሉ የኢትዮጵያ ወጣት ቡድን በበኩሉ ረጅም ኳሶችን ለአጥቂው ኦሜ መሐመድ በመላክ ለመጠቀም ሲጥር ታይቷል።

በጨዋታው መገባደጃ ላይ የኢትዮጵያ ተጫዋቾችን መዳከም ተከትሎ በተሻለ ወደግብ መድረስ የቻሉት ጋናዎች በኦሳቡቲይ እና አይዛክ ተውም አማካኝነት ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። በ88ኛው ደቂቃ አንድ የኢትዮጵያ ተጫዋች የህክምና ዕርዳታ ለማግኘት ከሜዳ በመውጣቱ የተፈጠረውን ክፍተት በመጠቀም የቴማ ዩዝ ክለብ አጥቂ የሆነው ጆናታን ኦሳቡቲይ ለጋና ወጣት ቡድን ትልቅ ዋጋ ያለው ግብ አስቆጥሯል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች የተደረጉ ሲሆን ከጋና ጆሴፍ ፓንሲል ከርቀት አክርሮ የመታው ከኢትዮጵያ ደግሞ ኦሜ መሐመድ በመስመር በኩል ወደግብ በመግባት የመታው እና ግብ ጠባቂው የያዘበት ኳስ የሚጠቀሱ ናቸው።

የመልሱ ጨዋታ ከሁለት ሳምንታት በኋላ በቅርቡ ተመርቆ በተከፈተውና አስራ አምስት ሺህ ተመልካቾችን መያዝ በሚችለው የኬፕ ኮስት ስታዲየም የሚደረግ ይሆናል። የኢትዮጵያ ወጣት ቡድን የደርሶ መልስ ጨዋታው አሸናፊ መሆን ከቻለ ለውድድሩ ለማለፍ ከቱኒዚያ እና ሴኔጋል አሸናፊ ጋር ይጫወታል።

Leave a Reply