ፕሪሚየር ሊግ ፡ ሀዲያ ሆሳዕና መውረዱን ሲያረጋግጥ አናት ላይ የተቀመጡት ነጥብ ጥለዋል

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 21ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በክልል ከተሞች ሲካሄዱ በደረጃ ሰንጠረዡ አናት የሚገኙ ክለቦች ነጥብ ጥለዋል፡፡ ንግድ ባንክ ደረጃውን ማሻሻሉን ሲቀጥል ሀዲያ ሆሳዕና ለከርሞ ወደ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ መውረዱን አረጋግጧል፡፡

ወደ ቦዲቲ ያቀናው መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ወላይታ ድቻ ጋር ባደረገው ጨዋታ ካለ ግብ አቻ ተለያይቷል፡፡ ከተከታዩ በ9 ነጥብ ርቆ የሊጉ አናት ላይ የተቀመጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ ቢጥልም ተከታዩ ኢትዮጵያ ቡናም ነጥብ በመጋራቱ የነጥብ ልዩነቱ እንደተጠበቀ ሆኗል፡፡ የወላይታ ድቻው ግብ ጠባቂ ወንድወሰን አሸናፊም 2ኛው ዙር ከተጀመረ ወዲህ መረቡን ሳያስደፍር ወጥቷል፡፡

ኢትዮጵያ ቡና ወደ ጎንደር ተጉዞ ከዳሽን ቢራ ጋር 2-2 አቻ ተለያይቷል፡፡ ግብ በማስቆጠር ቅድሚያውን የያዙት ዳሽን ቢራዎች ሲሆኑ በ26ኛው ደቂቃ ኤዶም ሆሶውሮቪ ግብ አስቆጣሪው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ቡና በ36ኛው ደቂቃ በሳዲቅ ሴቾ አማካኝነት አቻ በመሆን የመጀመርያውን አጋማሽ ሰያጠናቅቁ ከእረፍት መልስ በ52ኛው ደቂቃ በየተሻ ግዛው ግብ በድጋሚ መሪ መሆን ችለዋል፡፡ በ65ኛው ደቂቃ በጥሩ አቋም ላይ የሚገኘው ሳዲቅ ሴቾ ቡና አቻ ማድረግ ችሏል፡፡ ውዝግብ በበረከተበት ጨዋታ ጋቶች ፓኖም ከ ሳሙኤል አለባቸው ጋር ግጭት የፈጠሩ ሲሆን የሁለተኛው ጎል መቆጠሩን ተከትሎ የዳሽን ተጫዋቾች የዕለቱን ዳኛ በመክበብ በፈጠሩት ግርግር መሃል ከዳሽን ደጋፊዎች በተወረወረ ድንጋይ አርቢትር ዘካርያስ ግርማ የተፈነከቱ ሲሆን ህክምና እስኪደረግላቸው ጨዋታው ለመቋረጥ ተገዷል፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የዳሽን ደጋፊዎች ስርአት አልበኝነት እንደነበረና የኢትዮዽያ ቡና ደጋፊዎች በተወረወረው ድንጋይ ጉዳት እንደደረሰባቸው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡

ሆሳዕና ላይ ሀዲያ ሆሳዕና በ ንግድ ባንክ 2-0 ተሸንፎ ከፕሪሚየር ሊጉ መሰናበቱን አረጋግጧል፡፡ የንግድ ባንክን የድል ግቦች ከመረብ ያሳረፈው ናይጄርያዊው ፊሊፕ ዳውዚ ነው፡፡ ውጤቱን ተከትሎ ንግድ ባንክ ደረጃውን ወደ 4ኛ ከፍ ሲያደርግ ሀዲ ሆሳዕና በመጣበት አመት ወደ ታችኛው ሊግ መውረዱን አረጋግጧል፡፡

ይርጋለም ላይ ሲዳማ ቡና አዳማ ከተማን አስተናገዶ 1-0 በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሷል፡፡ የሲዳማ ቡናን የድል ግብ ከመረብ ያሳረፈው በክረምቱ የዝውውር መስኮት አዳማ ከተማን ለቆ ሲዳማ ቡናን የተቀላቀለው በረከት አዲሱ ነው፡፡

አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከተማ ደደቢትን በመርታት ላለውረድ ለሚደርገው ትግል ወሳኝ 3 ነጥቦች አግኝቷል፡፡ አርባምንጭ ከተማ በጸጋዬ አበራ የ17ኛ ደቂቃ ግብ ሲመራ ሳሙኤል ሳኑሚ ቡድኖቹ ወደ መልበሻ ክፍል ከማምራታቸው በፊት ደደቢትን አቻ አድርጓል፡፡ የአርባምንጭ ከተማን ወሳኝ የድል ግብ በ68ኛው ከመረብ ያሳረፈው አመለ ሚልኪያስ ነው፡፡ ውጤቱ አርባምንጭን ወደ 11ኛ ደረጃ ከፍ ሲያደርገው በ2ኛው ዙር ውጤት አልቀና ያለው ደደቢትን ወደ 8ኛ አውርዶታል፡፡

ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማ መከላከያን ሁለት ጊዜ የመምራት እድ ቢያገኝም ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል፡፡ ለድሬዳዋ ከተማ ፉአድ ኢብራሂም በ36ኛው ደቂቃ ሲያስቆጠር በ65ኛው ደቂቃ በሃይሉ ግማ ጡሩን አቻ አድርጓል፡፡ በላይ አባይነህ በ71ኛው ደቂቃ አስቆጥሮ ድሬዳዋን በድጋሚ መሪ ቢያደርግም መሃመድ ናስር በ90ኛው ደቂቃ መከላከያን አቻ ያደረገች ግብ አስቆጥሯል፡፡

ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ ኤሌክትሪክን 3-2 አሸንፎ ኤሌክትሪክን ወደ ወራጅ ቀጠናው መልሶታል፡፡ አስቻለው ግርማ በ3ኛው ደቂቃ ሀዋሳን ቀዳሚ ሲያደርግ ፒተር ኑዋዲኬ በ20ኛው ደቂቃ ኤሌክትሪክን አቻ ማድረግ ችሎ ነበር፡፡ ከእረፍት መልስ በ48ኛው እና 71ኛው ደቂቃ ፍርዳወቅ ሲሳይ የሀዋሳን መሪነት ወደ 3-1 ሲያሰፋው ደረጄ ሃይሉ በ86ኛው ደቂቃ ኤሌክትሪክን ከሽንፈት ልታደገች ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡

ሊጉ ሊጠናቀቅ የ5 ሳምንታት እድሜ ብቻ የቀረው ሲሆን ተአምር ካልፈጠረ በቀር ከተከታዩ በ9 ነጥቦች የራቀው ቅዱስ ጊዮርጊስ ለቻምዮንነቱ ተቃርቧል፡፡ ሀዲያ ሆሳዕና መውረዱን በማረጋገጡ ከሰንጠረዡ ወገብ በታች የሚገኙት ክለቦች በተለይም መከላከያ ፣ አርባምንጭ ከተማ ፣ ዳሽን ቢራ እና ኤሌክትሪክ ሀዲያ ሆሳዕናን ላለመከተል ብርቱ ትግል የሚጠብቃቸው ክለቦች ናቸው፡፡

የደረጃ ሰንጠረዥ

 

ከፍተኛ ግብ አግቢዎች

Leave a Reply