የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌድሬሽን ዛሬ ካይሮ በሚገኘው ዋና ፅህፈት ቤቱ የ2016 ኦሬንጅ ቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌድሬሽን ካፕ የምድብ ድልድልን ይፋ አድርጓል፡፡
በድልድሉ የተሳተፈው ብቸኛው የምስራቅ አፍሪካ ክለብ ያንግ አፍሪካንስ ብቻ ሲሆን ያንጋ በኮንፌድሬሽን ካፑ ምድብ አንድ ላይ ተደልድሏል፡፡
የ8 ጊዜ የአፍሪካ ሻምፒዮኑ አል አሃሊ ከዋይዳድ ካዛብላንካ እና በውድድር ዘመኑ ጥሩ ብቃት ላይ ከሚገኘው ከዛምቢያው ሻምፒዮን ዜስኮ ዩናይትድ ጋር ተደልድሏል፡፡ በምድብ ሁለት የ2014 የቻምፒየንስ ሊጉ አሸናፊ ኢኤስ ሴቲፍ ከዛማሌክ ኢኒምባ እና ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ጋር ተደልድሏል፡፡ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ወደ ድልድሉ የገባው በቅጣት ከውድድሩ ውጪ የተደረገው የዲ.ሪ. ኮንጎው ኤኤስ ቪታ ክለብን ተክቶ ነው፡፡
የካፍ ዲሲፕሊን ኮሚቴ የኮንጎ ሻምፒዮኖቹ ያልተገባ ተጫዋች በማሰለፋቸው ከቻምፒየንስ ሊጉ ምድብ ተሰናብተዋል፡፡ በ2015 የውድድር ዘመን ለማሊው ስታደ ማሊያን ተሰልፎ ሲጫወት ያልተገባ ባህርይ ያሳየው ማሊያዊው ኢድሪሳ ትራኦሬ አራት ጨዋታ ተቀጥቶ የነበረ ቢሆንም በ2016 መጀመሪያ ቪታን ተቀላቅሎ ከዚምባቡዌው ማፉንዞ ጋር በቻምፒየንስ ሊጉ ቅድመ ማጣሪያ ቀሪ የሶስት ጨዋታዎች ቅጣት እያለበት በመሰለፉ የኪንሻሳውን ክለብ ከምድቡ እንዲወጣ አድርጓል፡፡ የደቡብ አፍሪካው ሻምፒዮን ሰንዳውንስ ከኮንፌድሬሽን ካፑ በሚደአማ ተሸንፎ ቢወድቅም ቪታ ወደ ምድብ ያለፈው ሰንዳውንስን አሸንፎ ስለነበር ዳግም ወደ ቻምፒየንስ ሊጉ ሊመለስ ችሏል፡፡ በ2011 በተመሳሳይ ሁኔታ ቲፒ ማዜምቤ ያንቪየር ቢሳላን ባልተገባ ሁኔታ በማሰለፉ መቀጣቱ የሚታወስ ነው፡፡
በኮንፌድሬሽን ካፑ የዓምናው የቻምፒየንስ ሊግ አሸናፊው ቲፒ ማዜምቤ ከብቸኛው የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ ያንግ አፍሪካንስ እና ከጠንካራው የአልጄሪው ክለብ ኤምኦ ቤጃያ ጋር ተደልድሏል፡፡
የ2015 ኮንፌድሬሽን ካፕ ባለድሉ ኤቷል ደ ሳህል ከሶስት የሰሜን አፍሪካ ቡድኖች ጋር ተደልድሏል፡፡ ምድብ ሁለት ላይ የሚገኙት አራቱም ክለቦች ከሰሜን አፍሪካ ሲሆኑ በአጠቃላይ በሁለቱም ውድድሮች ላይ ከሚካፈሉት 16 ቡድኖች መካከል ዘጠኙ ከሰሜን አፍሪካ ናቸው፡፡
ቻምፒየንስ ሊግ
ምድብ 1 ፡ አል አሃሊ (ግብፅ) ፣ ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ (ሞሮኮ) ፣ አሴክ ሚሞሳስ (ኮትዲቯር) ፣ ዜስኮ ዩናይትድ (ዛምቢያ)
ምድብ 2 ፡ ኢኤስ ሴቲፍ (አልጄሪያ) ፣ ዛማሌክ (ግብፅ) ፣ ኢኒምባ (ናይጄሪያ) ማሜሎዲ ሰንዳውንስ (ደቡብ አፍሪካ)
ኮንፌድሬሽን ካፕ
ምድብ 1 ፡ ቲፒ ማዜምቤ (ዲ.ሪ. ኮንጎ) ፣ ሞሊዲያ ኦሎምፒክ ቤጃያ (አልጄሪያ) ፣ ያንግ አፍሪካንስ (ታንዛኒያ) ፣ ሚዲአማ (ጋና)
ምደብ 2 ፡ ኤቷል ስፖርቲቭ ደ ሳህል (ቱኒዚያ) ፣ ፋት ዩኒየን ስፖርት ራባት (ሞሮኮ) ፣ ካውካብ አትሌቲክ ክለብ ማራካሽ (ሞሮኮ) ፣ አል አሃሊ ትሪፖሊ (ሊቢያ)
ፎቶ፡ ሆሳም