የኢትዮዽያ ከሃያ አመት በታች ብሄራዊ ቡድን ከጋና ጋር ለሚያደርገው የመልስ ጨዋታ ከፊታችን እሁድ ጀምሮ ማረፊያውን በራስ አዳማ ሆቴል በማድረግ ዝግጅቱን ለማድረግ እንደወሰነ ሶከር ኢትዮዽያ ለማወቅ ችላለች፡፡
ባለፈው እሁድ ጋናን በአሜ መሃመድ ግቦች 2-1 የረቱት ተጫዋቾች በማግስቱ በክለባቸው ላለባቸው ጨዋታ የሄዱ ሲሆን ከጨዋታ መልስ በአዳማ ራስ ሆቴል እንደሚሰባሰቡ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በጋና ሞቃታማ የአየር ሁኔታ የሚጠብቃቸው በመሆኑ ለዝግጅት አዳማን እንደመረጡም ተነግሯል፡፡
ለመልሱ ጨዋታ በሚደረገው ዝግጅት በጋናው ጨዋታ የነበሩ የተወሰኑ ተጨዋቾች የሚቀነሱ ሲሆን በሱማልያው ጨዋታ ላይ የነበሩና ኋላ ላይ የተቀነሱ ተጨዋቾች በድጋሚ ጥሪ እንደቀረበላቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተያያዘ ዜና ከ20 አመት በታች ቡድኑ ከማሊ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን ጋር የወዳጅነት ጨዋታ በሚቀጥለው ሳምንት ለማድረግ ስምምነት የተደረሰ ሲሆን መቼ እና የት የሚለው ግን ገና አልታወቀም፡፡
የኢትዮጵያ ከ20 አመች በታች ብሄራዊ ቡድን በመልሱ ጨዋታ ወደ ተከታዩ ዙር የሚያሳልፈውን ውጤት ካሳካ በመጨረሻው የማጣርያ ዙር የሴኔጋል እና ቱኒዚያን አሸናፊ ይገጥማል፡፡