” ወደ ሱዳን የመመለስ ፍላጎት የለኝም ፤ ለደደቢት መፈረም የመጀመርያ ምርጫዬ ነው” አዲስ ህንፃ

የቀድሞው የዋልያዎቹ ኮከብ አዲስ ህንፃ ለሦስት አመት ከቆየበት ክለብ አልሀሊ ሸንዲ ጋር ባለመስማማት ወደ ሀገሩ ተመልሷል፡፡

በሼንዲ ያልተከፈለውን ደሞዝ ለማግኘት በክስ ሂደት ላይ የሚገኘው አዲስ በክለቡ ቀሪ ኮንትራት ቢኖረውም ወደ ሱዳን የመመለስ ፍላጎት እንደሌለው ተናግሯል፡፡

አዲስ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገውን አጭር ቆይታ እነሆ፡-

ህይወት በሱዳን እንዴት ነው?

በሱዳን ህይወት ጥሩ ነበር ፤ ጥሩ ጊዜም አሳልፌያለው፡፡ ሆኖም አሁን ባለው ሁኔታ ከክለቡ ጋር መቀጠል ስለማልችል ወደ ሀገሬ ተመልሻለው፡፡ ከመጣውም አንድ ወር ሆኖኛል፡፡

ከሼንዲ ጋር ያልተስማማህበት ምክንያት ምንድነው?

እግርኳሳዊ ምክንያት ሳይሆን አስተዳደራዊ ችግር ነው፡፡ ለአምስት ወር ያህል ደሞዜን አልከፈሉኝም፡፡

አምስት ወር ሙሉ ደሞዝ ያልከፈሉት ለምንድነው?

በጀት የላቸውም፡፡ የክለቡ ባለቤት ክለቡን የሚያስተዳድረው ግለሰብ መቀመጫው ሳውዲ አረብያ ነው፡፡ ከባለሃብቱ የሚለቀቀው ገንዘብ ባለመለቀቁ ምክንያት ደሞዝ አልተከፈለንም፡፡ የዚህ ችግር ተጠቂ እኔ ብቻ አይደለሁም፡፡ በርካታ ተጫዋቾች ደሞዝ ባይከፈላቸውም የኔን ከባድ የሚያደርገው በሰው ሀገር ያለ ደሞዝ መቀመጥ ነው፡፡ ሌሎቹ ሀገራቸው በመሆናቸው ሊቀልላቸው ይችላል ፤ ለኔ ግን በጣም በከባድ በመሆኑ ወደ ሀገሬ መጥቻለው፡፡

አሁን ጉዳዩ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

ክለቡን ከስሻለው፡፡ ለኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ደብዳቤ አስገብቻለሁ፡፡
የኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለሱዳን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሦስት ጊዜ ደብዳቤ ልኮ መልስ አልሰጡም፡፡ አሁን ለካፍ እና ለፊፋ የሚከፈል 400 ዶላር ከፍዬ ከወኪሌ እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመሆን ክሴን አቅርቤ መልስ እየጠበቅኩ ነው።

ስለቀጣይ የእግር ኳስ ህይወትህ ምን ታስባለህ?

በመጀመርያ የክሱን ጉዳይ መጨረስ አለብኝ፡፡ የአንድ አመት ከስድስት ወር ቀሪ ኮንትራት አለብኝ፡፡ ነገር ግን ውሳኔው ምንም ቢሆን ሱዳን ተመልሼ መጫወት አልፈልግም፡፡ መልቀቂያዬን በመያዝ ከቤተሰቤ ጋር ሆኜ በሀገሬ መጫወት ነው የምፈልገው፡፡

PicsArt_1464282061599

በቀጣይ በሀገር ውስጥ የምትቀላቀለው ክለብ ታውቋል?

አሁን ላይ ይሄ ነው ማለት ይከብዳል፡፡ ነገር ግን ማናችንም ወደተሻለ ቦታ መሄድ እንፈልጋለን፡፡

ወደቀድሞ ክለብህ ደደቢት ልትመለስ ትችላለህ?

እንደዛ ብዬ አስባለው፡፡ ደደቢት የመጀመርያ ምርጫዬ ነው፡፡ ቅድሚያ መጫወቱንም ለእነሱ እሰጣለው ፤ ይሳካል ብዬም አስባለሁ፡፡

PicsArt_1464282385697

(የቀድሞው የመድን እና ንግድ ባንክ አማካይ አዲስ ህንፃ በኢትዮጵያ ለመጨረሻ ጊዜ የተጫወተው ለደደቢት ነበር፡፡ ከ2004-2005 ለሁለት የውድድር ዘመናት በደደቢት ቆይቷል፡፡)

1 Comment

Leave a Reply