በዳሽን ቢራ እና ኢትዮጵያ ቡና ላይ የቅጣት ውሳኔ ተላለፈ

(ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የተላከ )

 

ግንቦት 14 ቀን 2008 ዓ.ም በዳሽን ቢራ እና በኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለቦች መካከል በተካሄደው የ2ኛው ዙር የኘሪሚየር ሊግ ጨዋታ ወቅት በጎንደር ስታዲየም የተከሰተውን የሰፖርታዊ ጨዋነት መጓደል የፌዴሬሽኑ የዲስኘሊን ኮሚቴ በጥልቀት ከመረመረ በኋላ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ የዳሽን ቢራ እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች በኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረሳቸው በክለቡ ላይ የ35,000.00 (ብር ሰላሳ አምስት ሺህ) የቅጣት ውሳኔ ተላልፏል፡፡ ዳሽን ቢራ በ2ኛው ዙር በሜዳው ከሚያደርጋቸው ቀሪ ጨዋታዎች መካከልም ሁለት ተከታታይ ውድድሮች ካስመዘገበው ሜዳ ውጭ በሚገኝ ገለልተኛ ሜዳ እንዲጫወት ተወስኗል፡፡

እንዲሁም የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ደጋፊዎች የዳሽን ቢራ ስፖርት ክለብ ደጋፊዎችን በዝማሬ ለፀብ ስለማነሳሳታቸው በመረጋገጡ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ 10,000.00 (አስር ሺህ ብር) ተቀጥቷል፡፡

የዲስኘሊን ኮሚቴው ከጨዋታ ታዛቢ በቀረበለት ሪፖርት መሠረት ክለቦች ደጋፊዎቻቸውን ስለ ስፖርታዊ ጨዋነት አስተምረውና ተመሳሳይ ጥፋት እንዳይፈፀም አስፈላጊውን አድርገው ውሳኔው በደረሳቸው በ15 ቀናት ውስጥ ሪፖርት እንዲያደርጉም አሳስቧል፡፡ የተወሰነባቸውን የገንዘብ ቅጣትም ይህ ውሳኔ በደረሳቸው በ15 የስራ ቀናት ውስጥ ለፌዴሬሽኑ ገቢ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

በተጨማሪም የእለቱ ዋና ዳኛ እና ረዳት ዳኛ እንዲሁም የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ቡድን መሪ እና ደጋፊዎች በደረሰባቸው ጉዳት ምክንያት ለሕክምና ያወጡትን ወጪ በሚያቀርቡት ማስረጃ መሠረት በዳሽን ቢራ ስፖርት ክለብ እንዲሸፈን በኮሚቴው ውሳኔ ተላልፎባቸዋል፡፡ ደጋፊዎችን ለፀብ በማነሳሳት ለዳኛው እና ለረዳት ዳኛው መፈንከት ምክንያት የሆነው የዳሽን ቢራ ተጫዋች ደረጀ መንግሥቱም አምስት ጨዋታ እና ብር 1,000.00 /አንድ ሺህ ብር/ ተቀጥቷል፡፡

 

በሌላ በኩል የዲስኘሊን ኮሚቴው የአዳማ ከነማ እግር ኳስ ክለብ በኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ንብረት ወድሞብኛል በማለት ያቀረበውን አቤቱታ መሠረት በማድረግ ግንቦት 18/2008 ዓ.ም የሁለቱንም ክለቦች መሪዎች ጠርቶ በማነጋገር ከውሳኔ በፊት ክለቦቹ ተወያይተው የደረሱበትን ስምምነት እስከ ግንቦት 24/2008 ዓ.ም እንዲያሳውቁ ማሳሰቢያ መሰጠቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

በመጨረሻም

የጨዋታው ታዛቢ አቶ ተስፋዬ ኦሜጋ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በማያሻማና ግልፀ በሆነ ሁኔታ የተብራራ ሪፖርት በማቅረባቸው ፣ የእለቱን ውድድር የመሩት ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ዘካሪያስ ግርማ፣ ረዳት ፌደራል ዳኛ አስቻለው ወርቁ ከዳሽን ቢራ ስፖርት ክለብ ደጋፊ በተወረወረ ድንጋይ ጉዳት ደርሶባቸው የእለቱን ውድድር ሳያቋርጡ በፅናት ውድድሩ እንዲጠናቀቅ በማድረጋቸው ፣

የዳሽን ቢራ ስፖርት ክለብ አመራሮች፤ የፀጥታ ኃይሎች፣ ችግሩን በቁጥጥር ስር ለማዋል ያላሰለሰ ጥረት በማድረጋቸው የጐንደር ዮኒቨርስቲ ሆስፒታል እና የቀይ መስቀል አባላት ለተጐዱ ሰዎች ላደረጉት አፋጣኝ የሕክምና እርዳታ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ እና የዲሲፒሊን ኮሚቴው ከፍተኛና የከበረ ምስጋና አቅርቧል፡፡

 

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሸን

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *