የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን በመጪው ግንቦት 28 በማሴሩ ከሌሶቶ ብሄራዊ ቡድን ጋር ለሚያደርገው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ዝግጅቱን ቀጥሏል፡፡
ዋልያዎቹ አዲስ አበባ ስቴድየም በግንቦት 20 ዝግጅት ምክንያት በመያዙ ትላንት ጠዋት መስራት የሚገባቸውን ልምምድ ሳይሰሩ የቀሩ ሲሆን አመሻሽ ላይ ሲኤምሲ በሚገኘው የንግድ ባንክ ሜዳ ላይ ለመስራት ተገደዋል፡፡
ብሄራዊ ቡድኑ ዝግጅቱን በመቀጠል ዛሬ ጠዋት በመከላከያ ሜዳ ልምምዱን የሰራ ሲሆን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ሱዳን የነበሩት ሳላዲን ፣ አስቻለው እና ምንተስኖት ከቡድኑ ጋር ዛሬ የመጀመርያ ልምምዳቸውን ሰርተዋል፡፡ በሃይሉ አሰፋንን በመተካት የተመረጠው ሽመክት ጉግሳ ደግሞ ትላንት ልምምዱን ጀምሯል፡፡ በህመም ምክንያት ሁለት የልምምድ ጊዜያት ያለፉት ጀማል ጣሳውም ከህመሙ ጋር እየታገለ ትላንት እና ዛሬ ልምምድ ሰርቷል፡፡
በአጠቃላይ 23 ተጫዋቾች በተሳተፉበት በዛሬው ልምምድ እንደከዚህ ቀደሙ ከኳስ ጋር ፈጣን እንቅስቃሴና ለሁለት ተከፍለው ግማሽ ሜዳ የተጫወቱ ሲሆን አቤል ማሞ በቀኝ እጁ ላይ በደረሰበት የጡንቻ መሳሳብ ምክንያት ልምምዱን አቋርጦ ሊወጣ ችሏል፡፡
ልምምዱ በዚሁ መልኩ ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን ሽመልስ በቀለ ነገ ፣ ጌታነህ ከበደ ደግሞ ሰኞ ቡድኑን ይቀላቀላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በተያያዘ ዜና ለብሔራዊ ቡድኑ አዲስ የህክምና ባለሙያ ተቀጥሯል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ እግርኳስ ክለብ እያገለገለ የሚገኘው በቀለ ዘነበ ከትላንት ጀምሮ ስራውን ጀምሯል፡፡