የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ከሌሶቶ ብሄራዊ ቡድን ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ ዝግጅቱን ቀጥሏል፡፡
የዋልያዎቹን የመጨረሻ የማጣርያ ጨዋታ በአምበልነት የመራው ሽመልስ በቀለ ትላንት አዲስ አበባ የገባ ሲሆን በዛሬው እለትም ከቡድኑ ጋር የመጀመርያ ልምምዱን ሰርቷል፡፡ ጌታነህ ከበደ ደግሞ ዛሬ አዲስ አበባ የሚገባ ሲሆን ነገ ከቡድኑ ጋር ይቀላቀላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የብሄራዊ ቡድኑ ጥሪ ከደረሳቸው 25 ተጫዋቾች መካከልም 24ቱ ልምምዳቸውን ሲሰሩ በጠባብ ሜዳ ውስጥ ክፍተት የማግኘት እና ጎል የማስቆጠር ልምምዶች እንዲሁም ለሁለት ተከፍለው መጫወት የዛሬ የልምምዳቸው አካል ነበር፡፡
ብሄራዊ ቡድኑ ኢንተርናሽናል የአቋም መለኪያ ጨዋታ ያላገኘ ሲሆን በነገው እለት ጠዋት ከኢትዮዽያ ንግድ ባንክ ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ እንደሚያደርጉ ታውቋል፡፡
አሰልጣኝ ገብረመድን እስካሁን ባለው ዝግጅት በጣም ደስተኛ እንደሆኑና በቡድኑ ቅንጅትና እንቅስቃሴ እንደተገረሙ እና ጥሩ ስራ እየሰሩ መሆኑን ለሶከር ኢትዮዽያ ተናግረዋል፡፡
ዋልያዎቹ በዕለተ ረቡዕ ወደ በደቡብ አፍሪካ ትራንዚት አድርገው ሌሶቶ የሚያመሩ ሲሆን እሁድ ግንቦት 28 ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡
ሶከር ኢትዮዽያ ነገ በብሄራዊ ቡድኑ ዝግጅት ዙርያ የተጨዋቾችን እና አሰልጣኞች አስተያየት ይዛ የምትቀርብ ይሆናል፡፡