የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ከሌሶቶ ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ ዝግጅቱን ቀጥሏል፡፡ የዝግጅቱ አካል በሆነው የዝግጅት ጨዋታም ዛሬ ረፋድ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ገጥመው 3-0 አሸንፈዋል፡፡
በርካታ ቁጥር ያለው የስፖርት ቤተሰብ በተከታተለው ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ ላይ በቋሚ አሰላለፉ ጀማል ጣሳው ፣ ያሬድ ባየህ ፣ አስቻለው ታመነ ፣ ስዩም ተስፋዬ ፣ አብዱልከሪም መሃመድ ፣ ጋቶች ፖኖም ፣ ኤልያስ ማሞ ፣ ምንተስኖት አዳነ ፣ ሽመልስ በቀለ ፣ ሳላዲን ሰይድ እና ዛሬ ቡድኑን የተቀላቀለው ጌታነህ ከበደ ተካተዋል፡፡ የመጀመርያው አጋማሽ ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ እና የጎል ሙከራ ሳይታይበት የተጠናቀቀ ሲሆን ሳላዲን ሰይድ በጉዳት ጨዋታውን አቋርጦ ወጥቷል፡፡
የሳላዲን የጉዳት አይነትና መጠን ከበድ ያለ እንደሆነና ለሌሶቶው ጨዋታ የመድረስ አለመድረሱ ጉዳይ ከህክምና በኀላ ቁርጡን እንደሚለይ ታውቋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ሙሉ ለሙሉ የተጨዋች ለውጥ ያደረጉ ሲሆን በመጀመርያው አጋማሽ ያልተሰለፉት ተጫዋቾች ገብተዋል፡፡ ግቦች የተቆጠሩትም በዚህኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሲሆን ታፈሰ ተስፋዬ 2 ፣ ዳዊት ፍቃዱ 1 ግብ ከመረብ አሳርፈዋል፡፡
ብሄራዊ ቡድኑ 18 ተጫዋቾችን ጨምሮ 28 የልኡካን ቡድን በመያዝ ነገ በደቡብ አፍሪካ በኩል አድርጎ ወደ ሌሶቶ ሲያመራ አቶ አበበ ገላጋይ የቡድን መሪ ሆነው ይጓዛሉ፡፡ በዛሬው እለትም የሚቀነሱ 7 ተጫዋቾች ይታወቃሉ፡፡
በብሄራዊ ቡድኑ ዙርያ ዛሬ 11:00 ላይ በኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡