በዛምቢያ አስናጋጅነት ለሚካሄደው የ2017 የአፍሪካ ከ20 አመት በታች ዋንጫ ማጣርያ ጋናን የሚገጥመው የኢትየጵያ ከ20 አመት ብሄራዊ ቡድን በአዳማ ከትሞ ዝግጅቱን ጀምሯል ፡፡
በመጀመርያው ጨዋታ አአ ስታድየም ላይ በአሜ መሃመድ ግቦች ተግዞ 2-1 ያሸነፈው ወጣት ቡድኑ ከሰኞ ጀምሮ ልምምዱን ይጀምራል ቢባልም ዘግይቶ ትላንት በአዳማ አበበ በቂላ ስታድየም ጀምሯል፡፡
ብሄራዊ ቡድናችን የዛሬውን የልምምድ ፕሮግራም ረፋድ ላይ ለማደረግ ቢያስብም ሜዳው በመያዙ ምክንያት ከ10:00 በኋላ ልምምዳቸውን ለመስራት ተገደዋል፡፡
በዛሬው ልምምዳቸው 20 ተጨዋቾች የተገኙ ሲሆን የውህደት ስራዎች እና በጠባብ ቦታ ውስጥ ኳስን ተረጋግቶ የመቀባበል ልምምድ ሲሰሩ ለማየት ችለናል፡፡
ከጉዳት ጋር በተያያዘ የጅማ አባቡናዎቹ ኪዳኔ አሰፋና ሱራፌል አወል መጠነኛ ጉዳት አጋጥሟቸው በዛሬው ልምምድ ያልተገኙ ሲሆን የጅማ አባ ቡናው ጀሚል የፓስፖርት ጉዳይ ለመጨረስ አዲስ አበባ በመሄዱ በዛሬው ልምምድ ላይ አልተገኘም፡፡
አዳማ ለዝግጅት የተመረጠው በጋና የሚጠብቃቸውን ሞቃታማ አየር ከወዲሁ ለመላመድ እንደሆነ ሲታወቅ ወደ ጋና እስኪሄዱ ድረስም በዚሁ እንደሚቆዩ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የተቀነሱ እና የተጨመሩ ተጫዋቾች
በጋና የመጀመርያው ጨዋታ ላይ ከነበሩት 23 ተጨዋቾች መካከል የወጣቶች አካዳሚው ግብ ጠባቂ ጆቤድ ፣ የደደቢቱ ቢንያም አበራ እና የዩኒቲ ጋምቤላው ጋድ ጋትኮች የተቀነሱ ሲሆን በምትካቸው የመከላከያው ቴዎድሮስ ታፈሰ ፣ የጅማ አባ ቡናው ጀሚል ያዕቆብ ፣ የአሶሳ ከተማው ዮሴፍ መርጋ ቡድኑን ተቀላቅለዋል፡፡
የአቋም መለክያ ጨዋታ
ከ20 አመት በታች ቡድኑ ከማሊ አቻው ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ እንዳገኘ አስታውቆ የነበረ ቢሆንም ከስምምነት ላይ መድረስ እንዳልቻሉ ተነግሯል፡፡ በምትኩም ከኢትዮዽያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ጋር ለመጫወት ቅድመ ሁኔታዎችን እያመቻቹ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል ።