ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሃገር ጋቦን ለምታስተናግደው የ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የሚደረጉ የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች ዛሬ መደረግ ይጀምራሉ፡፡ ለአራት ቀናት በሚደረጉ የማጣሪያ ጨዋታዎችም አላፊ ሃገራትን ይለያሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ዛሬ ቪክቶሪያ ላይ የምድብ 10 መሪዋ አልጄሪያ ሲሸልስን ትገጥማለች፡፡ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ አንድ ነጥብ ብቻ በቂዋ የሆነው አልጄሪያ ሲሸልስን በመጀመሪያው ጨዋታ ብሊዳ ላይ 4-0 የረታች ሲሆን ዛሬም የማሸነፉን ሰፊ ቅድመ ግምት አግኝታለች፡፡
ከአሰልጣኝ ክርስቲያን ጎርከፍ ጋር የተለያየው ብሄራዊ ቡድኑ በጊዜያዊ አሰልጣኘቹ ያዚድ መንሱሪ እና ነቢል ነግሃዚ እየተመራ ወደ ሜዳ ይገባል፡፡ ሪያድ ማህሬዝን እና ያሲን ብራሂሚን በጉዳት ኢስላም ስሊማኒን በቅጣት ያጡት የበረሃ ቀበሮዎቹ የኤል አረብ ሂላል ሱዳኒ መመለስ መልካም ዜና ሆኖላቸዋል፡፡
እስካሁን አንድም የማጣሪያ ጨዋታዎችን በሜዳዋ ያልተሸነፈችው ሲሸልስ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ ያከተመ ህልም ቢኖራትም ለክብር አልጄሪያን ለማሸነፍ ወደ ሜዳ ትገባለች፡፡
በሲሸልስ ስኬታማ ክለብ በሆነው ሴንት ሚሸል ክለብ አሰልጣኝነታቸው የሚታወቁት የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ራልፍ ጅያን ሉዊ በአውሮፓ የሚጫወቱ ተጫዋቾቻቸውን ለጨዋታው ጠርተዋል፡፡ የእግርኳስ ህይወታቸውን በጀርመን እየመሩ የሚገኙት ካርል ጄሮም ሆፕሪች እና ሉካስ ፖናዬ በቡድን ውስጥ ሲካተቱ ብሃራዊ ቡድኑ በሲሸልስ ሊግ ከሚጫወቱ የውጭ ሃገራት ተጫዋቾች ጋር ባደረገው የአቋም መለኪያ ጨዋታ ያለግብ አቻ ተለያይቷል፡፡ በአፍሪካ እግርኳስ በጣም የሰፋ ልዩነት ያላቸው ሁለቱ ሃገራት በዩኒቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ዛሬ የሚያደርጉ ይሆናል፡፡
ሀሙስ ግንቦት 25 ቀን 2008
18፡00 – ሲሸልስ ከ አልጄሪያ (ዩኒቲ ስታድየም)