የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከሌሶቶ ጋር ለሚያደርገው ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታ በሌሶቶ ዋና ከተማ ማሴሩ ይገኛል፡፡
ትላንት ጠዋት ከአዲስ አበባ ተነስቶ ጁሀንስበርግ የሁለት ሰአት ትራንዚት በማድረግ ሲሸልስ አመሻሹ ላይ የገባው ብሄራዊ ቡድናችን ዛሬ የመጀመርያ ልምምዱን ሰርቷል፡፡
በበረራ ፣ በሆቴል ፣ በመስተንግዶ እና አቅርቦት ረገድ ምንም አይነት ችግር እንደሌለና ቡድኑ የተለመደውን ዝግጅቱን እያደረገ መሆኑን አሰልጣኝ ገብረመድህን ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡
” ትላንት እንደሚታወቀው የእረፍት ቀን እንዲሆን በማሰብ ነበር ጉዞውን ያደረግነው፡፡ ዛሬ ረፋድ ላይ ከአንድ ሰአት በላይ የፈጀ ልምምዳችንን በጥሩ ሁኔታ ሰርተናል፡፡ ይህ ዝግጅታችን እስከ ጨዋታው መቃረቢያ ይቀጥላል” ብለዋል፡፡
ከጉዳት ጋር ተያይዞ እስካሁን ያጋጠመ ችግር የሌለ ሲሆን ዘግይቶ ቡድኑን ይቀላቀላል የተባለው ስዩም ተስፋዬ እስካሁን የመሄድ አለመሄዱ ጉዳይ አልታወቀም፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከሌሶቶ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ እሁድ 10:00 ላይ በማሴሩ ሴሴቶ ስታድየም ይካሄዳል፡፡