ጋቦን 2017 – አልጄሪያ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፏን አረጋግጣለች

ለ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ከምድብ 10 ሰፊ ግምት ተሰጥቷት የነበረቸው ሰሜን አፍሪካዊቷ ሃገር አልጄሪያ ዛሬ ቪክቶሪያ ላይ ሲሸልስን 2-0 በማሸነፍ ማለፏን አረጋግጣለች፡፡

ለማለፍ የአቻ ውጤት ብቻ በቂዋ የነበረው አልጄሪያ በጨዋታው ላይ የበላይነት የነበራት ሲሆን ከአምስት ጨዋታዎች 13 ነጥብ በመሰብሰብ በሚቀጥለው አመት ጥር ወር ለሚካሄደው የአፍረካ ዋንጫ ተሳትፎ ትኬቷን ቆርጣለች፡፡

የበረሃ ቀበሮዎቹ የሲሸልስን ግብ ለመድፈር ለ41 ደቂቃዎች የቆዩ ሲሆን ለፈረንሳዩ ሊል የሚጫወተው ያሲን ቤንዚያ የመጀመሪያውን ግብ ከመረብ አዋህዷል፡፡ ፈረንሳይ የተወለደው ቤንዚያ ለአልጄሪያ ለመጫወት የወሰነው በመጋቢት ወር አልጄሪያ ኢትዮጵያን ከመግጠሟ በፊት ቢሆንም ብሄራዊ ቡድኑ ባለው ጥልቅ የቡድን ስብስብ ምክንያት የቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ለመግባት እድል ሲያገኝ ይህ ለመጀመሪያ ግዜ ነው፡፡ ቤንዚያ ይህ ለአልጄሪያ ብሄራዊ ቡድን የመጀመሪያ የኢንተርናሽናል ጎሉም ናት፡፡ በማጥቃቱ በኩል ጠንካራ የነበሩት እንግዳዎቹ በሁለተኛው አጋማሽ በ62ኛው ደቂቃ ሂላል ኤል አረብ ሱዳኒ ባከላት ሁለተኛ ግብ ማሸነፍ ችለዋል፡፡ በጨዋታው ሲሸልስ አልጄሪያን ለመፈተን ስትቸገር ተስተውሏል፡፡

 

ከሌሶቶ ጋር በሜዳዋ አንድ ቀሪ ጨዋታ የሚቀራት አልጄሪያ ከወዲሁ አዘጋጇን ጋቦን እና ሞሮኮን በመከተል የአፍሪካ ዋንጫው ተሳታፊ ሁናለች፡፡


የዛሬ ውጤት

ሲሸልስ 0-2 አልጄሪያ


Leave a Reply