ጋቦን ለምታሰናዳው 31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የሚደረጉ የምድብ ጨዋታዎች ትላንት በሶስት ጨዋታዎች ቀጥለው ሲደረጉ ካሜሮን ወደ አፍሪካ ዋንጫ መመለሷን ያረጋገጠችበትን ጣፋጭ ድል ናውኩቾ ላይ ተቀዳጅታለች፡፡ ቱኒዚያ ምስራቅ አፍሪካዊቷን ሃገር ጁቡቲን በቀላሉ ስትረታ ቱኒዝ ላይ ሊቢያ እና ሞሮኮ አቻ ተለያይተዋል፡፡
በዕለቱ ታላቅ ጨዋታ በምድብ ማጣሪያው በሜዳዋ ሽንፈትን ያላስተናገደችው ሞሪታንኒያ በካሜሮን 1-0 ተሸንፋለች፡፡ ሁለቱ ሃገራት በነበራቸው ጠባብ የነጥብ ልዩነት ምክንያት ጨዋታው ሲጠበቅ የነበረ ሲሆን የማይበገሩት አንበሶች ማሸነፋቸውን ተከትሎ ደቡብ አፍሪካ ከአፍሪካ ዋንጫው ውጪ ሆናለች፡፡ የካሜሮንን የድል ግብ የመስመር አማካዩ ኤድጋር ሳሊ በግሩም ሁኔታ ከፍፁም ቅጣት ምት ውጪ አክርሮ የመታት ኳስ በ31ኛው ደቂቃ ወደ ግብነት ተቀይራለች፡፡ ሞሪታኒያ በሁለተኛው አጋማሽ ተከላከዩ ሙስጠፋ ዲያው በቀይ ካርድ በሜዳ በመውጣቱ በ10 ተጫዋች ለመጫወት ተገደዋል፡፡
ምድብ 13ን ካሜሮን በ11 ነጥብ ስትመራ ሞሪታንያ በሰባት ትከተላለች፡፡
ጅቡቲ አሁንም በሜዳዋ ተሸንፋለች፡፡ ቱኒዚያ ጅቡቲን 3-0 በማሸነፏ የምድብ አንድ አላፊ ሃገርን ለመለየት የግድ የመጨረሻ የምድብ ጨዋታዎችን መጠበቅ ግድ ብሏል፡፡ የካርቴጅ ንስሮቹን የድል ግቦች ናይም ስሊቲ፣ ሃምዲ ሃሮቢ እና በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ጣሃ ያሲን ኬኒሲ በስማቸው አስመዝግበዋል፡፡ ጁቡቲዎች በምድብ ማጣሪው ለሁለተኛ ግዜ ግብ ማስቆጠር የሚችሉበትን እድል የግብ አግዳሚ አምክኖባቸዋል፡፡ ድሉን ተከትሎ ቱኒዚያ የምድቡን መሪነት በግዜያዊነት ከላይቤሪያ ተረክባለች፡፡
ምድቡን ቱኒዚያ በ10 ነጥብ ስትመራ እሁድ ቶጎን የምትገጥመው ላይቤሪያ 9 ነጥብ በመሰብሰብ ሁለተኛ ነች፡፡ በክላውድ ለርዋ መሰልጠን የጀመረችው ቶጎ ሰባት ነጥብ አላት፡፡
ሊቢያ ወደ አፍሪካ ዋንጫው የማለፍ ተስፋዋን ከሞሮኮ ጋር 1-1 በመለያየቷ መና አስቀርታዋለች፡፡ በመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥር ስኬታማ የነበሩት የአትላስ አንበሶቹ በነቢል ድራር ግብ 1-0 መምራት ችለዋል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ አጥቅተው የተጫወቱት ሊቢያዎች በሳናድ ኦርፈሊ የጭማሪ ሰዓት ግብ አቻ ለመለያየት ችለዋል፡፡
እስካሁን በተደረጉ ጨዋታዎች ካሜሮን፣ አልጄሪያ እና ሞሮኮ አዘጋጇን ጋቦንን ተከትለው ለአፍሪካ ዋንጫው የሚወስዳቸውን ትኬት ቆርጠዋል፡፡
የአርብ ውጤቶች
ጁቡቲ 0-3 ቱኒዚያ
ሞሪታንያ 0-1 ካሜሮን
ሊቢያ 1-1 ሞሮኮ