ኢትዮጵያ ሌሶቶን በማሸነፍ በጥሩ 2ኘነት ለማለፍ የምታደርገውን ትግል አጠናክራለች

ዛሬ በተደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ኢትዮጵያ ሌሶቶን 2-1 በመርታት ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የምታደርገውን ትግል አጠናክራለች፡፡

በጨዋታው መጀመርያ ደቂቃዎች በፈጣን ቅብብል ወደ ሌሶቶ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ዋልያዎቹ በ10 ደቂቃዎች ውስጥ ብቻ በሽመክት ጉግሳ ፣ ጌታነህ ከበደ እና ዳዊት ፍቃዱ አማካኝነት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገው በግብ ጠባቂው ጄሉስ ከሽፎባቸዋል፡፡

ጨዋታው እየተጋመሰ ሲሄድ ኢትዮጵያውያን መቀዛቀዝ የጀመሩ ሲሆን እንቅስቃሴውም ተመጣጣኝ ሆኗል፡፡

የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ሴኮንዶች ሲቀሩ ጌታነህ በረጅሙ የተሻገረው ኳስ ሲመለስ ጀርባውን ለጎሉ ሰጥቶ በመቆጣጠር አዙሮ የመታው ኳስ በግሩም ሁኔታ ከመረብ አሳርፏል፡፡ በኢትዮጵያ መሪነትም ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ ሌሶቶዎች ሳይጠበቁ ጠንክረው የቀረቡ ሲሆን ጫና የፈጠረ እንቅስቃሴም ማድረግ ችለዋል፡፡

በ53ኛው ደቂቃ ጌታነህ ከበደ የሌሶቶ ተከላካዮች የፈጠሩትን ሰህተት ተጠቅሞ ያገኘውን ኳስ የግብ ክልሉን ለቆ በወጣው ግብ ጠባቂ አናት በመምታት በግሩም ሁኔታ አስቆጥሯል፡፡

PicsArt_1465144778702

የጌታነህ ግብ የሌሶቶን ጫና ይቀንሳል ተብሎ ቢጠበቅም ከ3 ደቂቃዎች በኋላ ጄን ታባ-ኒትሶ በቮሊ ባስቆጠረው ግብ ሌለሶቶች ወደ ጨዋታው ተመልሰዋል፡፡

ጎሉን ተከትሎ ሌሶቶዎች የበለጠ ጫና ለመፍጠር ሲሞክሩ አሰልጣኝ ገብረመድህን የመከላከል ባህርይ ያላቸው አማካዮችን ቀይሮ በማስገባት ውጤቱን ለማስጠበቅ ጥረት አድርገዋል፡፡ በመጨረሻም ተሳክቶላቸው ጨዋታው በኢትዮጵያ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ድሉ ኢትዮጵያን በ8 ነጥብ 2ኛ ደረጃዋን እንድታጠናክር ሲያደርጋት በጥሩ ሁለተኝነት ለማለፍ ከሌሎች ምድቦች ጋር የምታደርገውን ፉክክር ቀጥላለች፡፡

PicsArt_1465144838931

አሰልጣኝ ገብረመድህን ሃይሌ በመጀመርያ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነታቸው ድል ሲያስመዘግቡ ለመጀመርያ ጊዜ ዋልያዎቹን በአምበልነት የመራው ጌታነህ ከበደ በአስደናቂ የግብ ማስቆጠር አቋሙ ቀጥሏል፡፡ ጌታነህ ባለፉት 5 የብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎች 7 ግቦች ከመረብ ማሳረፍ ችሏል፡፡

በጨዋታው በርካታ ኢትዮጵያውያን በስታድየም በመገኘት ዋልያዎቹን ሲደግፉ ታይቷል፡፡

 

1 Comment

Leave a Reply