“አቋሜን ጠብቄ ብሄራዊ ቡድኑን ለረጅም ጊዜ ማገልገል እፈልጋለው” አህመድ ረሺድ

የኢትዮዽያ ብሄራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ 5ኛ ጨዋታውን እሁድ ከሌሶቶ ጋር አድርጎ 2-1 አሸንፎ ተመልሷል፡፡ በእለቱ የመጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ የተካተተው አህመድ ረሺድ በዋልያዎቹ ማልያ የመጀመርያ ጨዋታውን ማድረግ ችሏል፡፡

“ሽሪላ”  ብሄራዊ ቡድኑ ትላንት ምሽት አዲስ አበባ በደረሰበት ወቅት ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው ቆይታ ጨዋታውን ማሸነፍ ይገባቸው እንደነበር ገልጿል፡፡

“ጨዋታው በጣም ጥሩ ነበር፡፡ ከመጀመርያው አጋማሽ ጀምሮ በደንብ ተቆጣጥረን ነበር የተጫወትነው፡፡ ማሸነፍ ይገባን ነበር ፤ ከፈጣሪ ጋር አሸንፈን ወጥተናል፡፡ ” ይላል፡፡

ከዚህ ቀደም ለኢትዮጵያ ከ23 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን የተጫወተው አህመድ የብሄራዊ ቡድን የመጀመርያ ጨዋታውን ከዚህ ቀደሙ ልምዱ በማነፃፀር የጎላ ልዩነት እንደሌለው ይገልፃል፡፡

” ያን ያህል ብዙ ልዩነት የለውም፡፡ የደረጃ ወይም የእድሜ ተዋረድ ነው እንጂ ብዙም ልዩነት የለውም፡፡ ትንሽ የሚለየው ዋናው ብሄራዊ ቡድን ላይ ስትመጣ ብዙ ሲኒየሮችን ነው የምታየው ፤ ያ ደግሞ ከልምዳቸው  ብዙ እንድትማር ያደርግሃል፡፡ ”

በ2007 የውድድር ዘመን በቡና ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ሰብሮ ከገባ በኋላ ቦታውን ማስከበር የቻለውና በሊጉ ከሚጠቀሱ ጥቂት ድንቅ የመስመር ተከላካዮች አንዱ የሆነው አህመድ የብሄራዊ ቡድን ጥሪው ስለመዝገየቱ አሰቦ እንደማያውቅ ይናገራል፡፡

“እእ . . . መቼም ሁሌም ጠንክረህ ስራህን አክብረህ ከሰራህ የፈጣሪ ፍቃድ ሆኖ የልፋትህን ታገኛለህ፡፡ የብሄራዊ ቡድን ጥሪ በሰአቱ መጥቷል ፣ ዘግይቷል ፣ ቸኩሏል ብዬ የማስበው ነገር የለም፡፡ በጊዜው ስለመጣ  ፈጣሪዬን አመሰግነዋለው ” ብሏል፡፡ አክሎም የብሄራዊ ቡድን ቦታውን አስከብሮ ለመቀጠል ጠንክሮ እንደሚሰራ ተናግሯል፡፡

” አሁን ካለኝ ብቃት የተሻለ ነገር እሰራለው ብዬ ነው የማስበው፡፡ ቋሚነቴንም ለማግኘት እጥራለው፡፡ በእግርኳስ ወደፊት የሚፈጠረውን አናውቀውም ፤ ጉዳት እና የተለያዩ ነገሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ ከፈጣሪ ጋር አቋሜን ጠብቄ ብሄራዊ ቡድኑን ረጅም ጊዜ ማገልገል እፈልጋለው፡፡ ” ሲል ሀሳቡን አጠቃሏል፡፡

PicsArt_1465289725748

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *