በ21ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጎንደር ላይ ዳሽን ቢራ ከ ኢትዮጵያ ቡና ባደረጉት ጨዋታ ለተከሰተው የደጋፊዎች ጉዳት ተጠያቂ የተደረገው ዳሽን ቢራ በሜዳው የሚያደርጋቸውን ሁለት ጨዋታዎች በገለልተኛ ሜዳ እንዲያደርግ ፌዴሬሽኑ መቅጣቱ ይታወሳል፡፡
በተወሰነው ውሳኔ ላይ የዳሽን ቢራ ስፖርት ክለብ ይግባኝ ያቀረበ ቢሆንም ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው ተቀብሎ ከመረመረ በኋላ ይግባኙን እንደማይቀበለውና ውሳኔው በመፅናቱ ምክንያት ዳሽን ቢራ የሚጫወትበትን ገለልተኛ ሜዳ እንዲያሳውቅ ተወስኗል፡፡
በዚህም መሰረት ዳሽን ቢራ የሚጫወትበትን ሜዳ አዳማ አበበ በቂላ ስታድየም እንዲሆን ባቀረበው ጥያቄ መሰረት የኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጥያቄውን መቀበሉን ከፌዴሬሽኑ ህዝብ ግንኙነት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ውሳኔውን ዳሽን ቢራ በ23ኛው ሳምንት ከአርባምንጭ ከተማ እንዲሁም መጨረሻው ሳምንት ከሲዳማ ቡና የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም ያደርጋል፡፡
ላለመውረድ በሚደረገው ትግል ውስጥ የሚገኘው ዳሽን ቢራ ቀሪዎቹን 5 ጨዋታዎች ከከተማው ርቆ አዲስ አበባ (2) ፣ ሀዋሳ (1) እና አዳማ (2) ላይ ማድረጉ ሌሎች የመውረድ ስጋት ካላቸው ክለቦች አንጻር ጫና ይፈጥርበታል፡፡