የጎ-ቴዲ ፉትሳል ዋንጫ ዛሬ ተጀምሯል

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የፉትሳል ኮሚቴ የ2008 ዓ.ም የፉትሳል ዋንጫ ውድድሩን ከጎ-ቴዲ ስፖርት ጋር በመተባበር ዛሬ የመክፈቻ ጨዋታዎችን በብሄራዊ የወጣቶች ስፖርት አካዳሚ አከናውነዋል፡፡

ስምንት ቡድኖች በሚሳተፉበት ይህ ውድድር ዛሬ በመጀመሪያ የጨዋታ መርሃ ግብሩ አበበ ቢቂላን ከሊና ሆቴል ሲያገናኝ ጨዋታው በሊና ሆቴል 8-7 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ለአበበ ቢቂላ ሚካኤል ክንፈ፣ሄኖክ ብርሃኑ፣ኀይትኦም ንጉሴ፣ሃሪቤል በቀለ፣አሸናፊ ግርማ(2)፣ሰዒድ ኪያር ግቦቹን ሲያስቆጥሩ ለሊና ሆቴል ብስራት ሽፈራው(2)፣ተስፋሁን አበራ(3)፣ዳንኤል ደሳለኝ፣አበራ ታደሰ(2) የአሸናፊነቱን ጎሎች አስቆጥረዋል፡፡

እንደ አሸናፊ ግርማ የመሳሰሉ የቀድሞ ዝነኞችን የያዘው አበበ ቢቂላ በጨዋታው ከተጋጣሚው የተሻለ መንቀሳቀስ ቢችልም ጨዋታውን ማሸነፍ ግን አልቻለም፡፡

በሁለተኛው ጨዋታ ቲጂና ጓደኞቹ ከኪምብሪያ ኢትዮጵያ ጋር ያገናኘው ጨዋታ የስፖርት ቤተሰቡን ያዝናና እና ቁጭ ብድግ ያደገረ ጨዋታ ተስተውሏል፡፡ ድንቅ ፉክክር በታየበት እና ብዙ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ የምናቃቸውን ተጨዋቾች ያየንበት የነዚህ ሁለት ቡድኖች ጨዋታ 5-5 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡ ለቲጂ እና ጓደኖቹ ለሚ ኢታና(2) ፣ መሃመድ ወርቁ (2) እና ሲሳይ ነጋሽ ጎሎችን ሲያስቆጥሩ ለኪምብሪያ ኢትዮጵያዎች በድንቅ የጨዋታ እንቅስቃሴ ክፍሎም ገ/ክርስቶስ ፣ ብሌን ጌታቸው(2) ፣ ወሳኝ ገብሬ እና ከሃሊ ጌታነህ አስቆጥረዋል፡፡

ውድድሩ በመጪው ረቡዕ ሲቀጥል በ2፡30 ኢኤስኤፍ ከአሴጋ ይጫወታሉ፡፡  3፡30 ላይ ደግሞ ጂኬ ኢትዮጵያ ከብሉቤል ኮምፒዩተር ይጫወታሉ፡፡ 4፡30 አበበ ቢቂላ ከቲጂና ጓደኞቹ ሲጫወቱ በእለቱ የመጨረሻ መርሃ ግብር የሆነው የሊና ሆቴል እና የኪምብሪያ ኢጥዮጵያ ጨዋታ 5፡30 የሚከናወን ይሆናል፡፡

የስፖርት ቤተሰቡም ገርጂ አካባቢ በሚገኘው ብሄራዊ የወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በመገኘት ቡድኖቹን እንዲያበረታታ የፉትሳል ኮሚቴው ይጋብዛል፡፡

Leave a Reply