“አሁን ባይሆንም በሶስት እና አራት አመታት ውስጥ ክለቦች የራሳቸው አካዳሚዎች ሊኖሯቸው ይገባል” ዴቪድ በሻ

ትውልዱ በኮሎኝ ከተማ ጀርመን ነው፡፡ ከኢትዮጵዊ አባት እና የጀርመን እናት የተገኘው የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እና ኢትዮጵያ ቡና ተጫዋች ዴቪድ በሻ፡፡

ዴቪድ ደቡብ አፍሪካ ባዘጋጀችው የ2013ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የዋልያዎቹ ቡድን አባል የነበረ ሲሆን በ27 ዓመቱ በደረሰበት የጉልበት ጉዳት ምክንያት ከሚወደው እግርኳስ ለመለየት ተገዷል፡፡

በስፖርት አስተዳደር ዲፕሎማ ያለው የመስመር ተከላካዩ አሁን የስፖርት አማካሪ እና የተጫዋች ወኪል ሆኖ ብቅ ብሏል፡፡ ዴቪድ አሁን ስለከፈተው ቢዝነስ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ከተጫዋችነት ወደ እግርኳስ ቢዝነስ ለመግባት ያደረከውን ሽግግር እንዴት ትመለከተዋለህ?

ያደረኩት ሽግግር በጣም ፈጣን ነበር፡፡ ነገር ግን በቶሎ አቅጄ የጀመርኩት ነገር ሳይሆን የረጅም ጊዜ እቅዴ ነበር፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ ኳስ መጫወት ካቆምኩ በኃላ ወደዚህ ቢዝነስ መሰማራት እፈልግ ነበር፡፡

እግርኳስ ከሁለት አመታት በኃላ አቆማለው ብዬ አላሰብኩም ያው የህይወት ነገር ስለሆነ ነው ያቆምኩት፡፡ በመጀመሪያ በቡና ስጫወት ሜዳ ውስጥ ብቻ ያለው ነገር  ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ነገሮች መታዘብ ችያለው፡፡ ከእነሱ ጋር አብረን ለመስራት ጥያቄ አቅርቤ ነበር ልንስማማ ባንችልም፡፡ ያው ከዚያ የራሴን የእግርኳስ አማካሪ ድርጅት ልከፍት ችያለሁ፡፡

በመጀመሪያ ስጀመር የተጫዋቾች ወኪል መሆን ፍላጎቴ አልነበረም፡፡ ውጪ የማውቃቸው ተጫዋቾች ጥያቄ ስለሚያቀርቡልኝ ወደ ቢዝነሱ ብገባ ትርፋማ እሆናለው ፣ ለኢትዮጵያ እግርኳስም በጎ ነው ብዬ በማሰቤ ወደ ስራው ገብቻለው፡፡

በድርጅትህ ውስጥ የሚሰሩ ስራዎች ምንምን ናቸው?

በተለያዩ ነገሮች ላይ ድርጅቴ ይሰራል፡፡ የማስታወቂያ፣ የማርኬቲንግ ምክሮች እና የተጫዋች ወኪልነት የሚሰጡ አገልግሎቶች ናቸው፡፡

በውጭ ሃገር የሚጫወቱ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን የሚመለከት ዳታ ቤዝ እያዘጋጀን ነው፡፡ ከውጭ ተጫዋቾች ጋር ግንኙነት መፍጠር ምንያህል ለፌድሬሽኑ ከባድ እንደሆነ ስለማውቅ፡፡

አውስትራሊያ ከሚገኝ የትጥቅ አማራች ድርጅት (ኤኤምኤስ ክሎዚንግ) ጋር በመተባበርም ለክለቦቻችንን እና ለብሄራዊ ቡድኑ ትጥቅ ለማቅረብ ድርድሮች እያደረግን ነው፡፡ እስካሁን የተጠናቀቀ ድርድር ባይኖርም ከተለያዩ ክለቦች ጋር ድርድሮችን በጥሩ ሁኔታ እያደረግን ነው፡፡

አንተ ያደግከው አውሮፓ ነው፡፡ የእግርኳሱ ባህል ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት ክፍለ ዓለም አብዛኛውን ህይወትህን አሳልፈሃል፡፡ የኢትዮጵያ እግርኳስ ደግሞ በልማዳዊ አስተሳሰቦች የሚጓዝ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ቢዝነሶች ምን ያህል አዎንታዊ ለውጥ ያመጣሉ ብለህ ታስባለህ?

እግርኳሱ ገና ታዲጊ ነው፡፡ የታዳጊዎች ማሰልጠኛ ደግሞ ትክክለኛው እግርኳሱን መለወጥ የሚቻልበት አካሄድ ነው፡፡ ድርጅቴም የዚህ ሃሳብ ደጋፊ ነው፡፡ ብዙ ስራዎች መሰራት አለባቸው፡፡ እኔ ራሴን የዚሁ ተግባር አካል ሆኜ ማገዝ እፈልጋለው፡፡ ጀርመን በመወለዴ በዛ ያለኝን ግንኙነት በማጥበቅ ጥሩ ስራዎችን በድርጄቴ በኩል የመስራት አቅሙም ፍላጎትም አለኝ፡፡ በእግርኳስ ከግራስሩትስ ብቻ አትጀምርም የሃገሪቱን ተጨባጭ የእግርኳስ ደረጃ መመልከትም ያስፈልጋል፡፡ በሁለቱ መካከል መመጣጠን ያስፈልጋል፡፡ በታዳጊዎች ስልጠና ላይ ሚሊዮኖች አፍስሰን ለ15 ዓመታት መጠበቅ አለብን ብለህ የምታናበት አይደለም፡፡ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ እና በታደጊዎች ስልጠና ላይ መመጣጠን ያስፈልጋል፡፡

በውጪ ሃገር የሚጫወቱ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾችን በሚመለከት ዳታ ቤዝ በመስራት ላይ እንደምትገኘ ነግረሃናል፡፡ ከ2011 በኃላ በተለይ ኢትዮጵያን የመወከል ፍላጎቱ በውጪ በሚጫወቱ ተጫዋቾች ላይ እያየለ መጥቷል፡፡ አንተ፣ ፉአድ ኢብራሂም፣ የሱፍ ሳላ እና ዋሊድ አታ በቅርብ ግዜያት የብሃራዊ ቡድኑን መለያ መልበስም ችሏችኋል፡፡
ልክ እንደሌሎቹ የአፍሪካ ሃገራት ኢትዮጵያ ብቁ የሆኑትን ትውልደ ኢትዮጵዊያን ለመሳብ ለምን አልቻለችም ?

ችግሩ የሚመነጨው በፌድሬሽኑ እና በተጫዋቾች መካከል አገኛኝ ድልድይ አለመኖሩ ነው፡፡ ግንኙነት የለም ማለት ይችላል፡፡ የኔም አንዱ ስራ ፌድሬሽኑን እና እነዚህን ተጫዋቾች ማገናኘት ነው፡፡ በተጨማሪም ፌዴሬሽኑ ተጫዋቾቹን ጠርቶ የማጫወቱ ፍላጎት የለውም፡፡ ተጫዋቾቹ የመጫወት ፍላጎት ቢኖራቸውም ሁሉም ለብሄራዊ ቡድኑ ይመጥናሉ ማለት አይደለም፡፡ የሃገር በቀሎችንም መርሳት የለብንም፡፡ ፍላጎቱ ካላቸው ብቃታቸውን አይተን መጥራት ወይም መተው እንችላለን፡፡

PicsArt_1466180718184

በታዳጊዎች ስልጠና ላይ አፅኖት ሰጥተህ ትናገራለህ፡፡ ለኢትዮጵያ እግርኳስ አዋጪው መንገድ በአንተ አስተሳሰብ የትኛው ነው?

በአንድ ጊዜ የአውሮፓ ደረጃ ላይ መድረስ አይቻልም፡፡ ከአንድ ቦታ ስትጀምር ነው ለውጥ የሚመጣው፡፡ ይህ ለውጥ ደግሞ መምጣት ያለበት ከፌድሬሽኑ ነው፡፡ ከዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ክለቦች የሴት ቡድን እንዲኖራቸው ፌድሬሽኑ ግዴታ አውጥቶ ነበር፡፡ አሁን ስትመለከት አብዛኛዎቹ የፕሪምየር ሊግ ክለቦች የሴት ቡድን አላቸው፡፡

አሁን በፍጥነት ባይሆንም በሶስት እና አራት አመታት ክለቦች የራሳቸው የማሰልጠኛ አካዳሚዎች ሊኖሯቸው ይገባል፡፡ በርግጥ ክለቦቹ ይህንን ብቻቸውን ሊሰሩት አይችሉም ፤ እገዛን ይሻሉ፡፡ ፌድሬሽኑ ላይ ብዙ ስራዎች መሰራት አለባቸው፡፡ እንደሰማሁት ከሆነ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብረ ዘይት ላይ አካዳሚ እንደገነባ ነው፡፡ ይህ ጥሩ ጅምር ነው፡፡ ነገር ግን ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት እንደዚህ አይነት ስራዎችን መስራት ያለበት እና ዋነኛ ተዋናዩ ፌድሬሽኑ መሆን መቻል አለበት፡፡

በጀርመን የተሰራው ይህ ነው፡፡ አስታውሳለው በዩሮ 2000 ከምድብ በአሳፋሪ መልኩ ነበር የወደቀችው፡፡ ከዛ በኃላ በተሰሩ ስራዎች በ14 ዓመታት ውስጥ ምን ያህል ለውጥ እንደመጣ ማየት ችለናል፡፡ ሁሉም ክለቦች አካዳሚ ቢኖራቸው እና ከሰባት እና ስምንት አመት እድሜያቸው ጀምሮ ተገቢውን ስልጠና ቢያገኙ ጥሩ ጅምር ይሆናል፡፡

ጋቶች ፓኖም እና ፊሊፕ ዳውዝ ከወዲሁ በአንተ ኤጀንሲ ስር ናቸው፡፡ ከአውሮፓ ካለህ የጠበቀ ግንኙነት ተነስተን ቀጣይ ማረፊያቸው አውሮፓ ይሆነናል ብለን መገመት እንችላለን?

ፊሊፕ ከንግድ ባንክ ጋር ያለው ውል ዘንድሮ ይጠናቀቃል፡፡ ለፊሊፕ በሚቀጥለው አመት ከኢትዮጵያ ውጪ የሚጫወትበትን ዕድል እያመቻቸን ነው፡፡ ድርድሩ በሂደት ላይ ስለሆነ የት እንደሆነ አሁን መግለፅ አልችልም፡፡ ግብፅ ሄዶ ሙከራ እንዳደረገ አውቃለው፡፡ ነገር ግን ንግድ ባንክ እና የግብፁ ክለብ በዝውውር ገንዘብ ባለመስማማታቸው ዝውውሩ እውን ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ጋቶች ለኔ በጣም ጥሩ ተጫዋች ነው፡፡ ወደፊት ጥሩ ደረጃ ላይ መድረስ የሚችል ተጫዋች ነው፡፡ የቡና እና የብሄራዊ ቡድኑ ወሳኝ ተጫዋችም መሆን ችሏል፡፡ ካለው አቅም አንፃር በውጪ ሊጎች የመጫወት አቅም አለው፡፡

በጉዳት ምክንያት ገና መጫወት እየቻልክ ነው ጫማህን የሰቀልከው፡፡ ተመልሶ የመጫወቱ ሀሳብ አሁንም በውስጥ አለ?

(ሳቅ) እንዳልከው በጉልበት ጉዳት ምክንያት ከኳሱ አለም ተገልያለው፡፡ ጉልቤቴ ላይ ቀዶ ጥገና አድርጌ ለ10 ወራት ከሜዳ ርቄ ነበር፡፡ የህይወቴ በጣም ከባዱ ግዜ ነበር፡፡ ስለማቆም አለሳብኩም ነበር ግን በጉዳት ላይ እያለው ከኳስ በኃላ ስላለው ህይወቴ ማሰብ ነበረብኝ ለማቆም አልቸገረኝም፡፡ ኳስ ካቆምኩ በኃላ ስለምሰራው ስራ ቀድሜ በማወቄ ነገሮችን አቅልሎልኛል፡፡ አዎ ስታዲየም ስመጣ በተለይ ቡና ሲጫወት እንደገና ወደ ሜዳ የመመለስ ፍላጎት ያድርብኛል፡፡ ቢሆንም አሁን ባለኝ ስራ የሃገሪቱን እግርኳስ በደንብ ማገዝ እችላለው፡፡

Leave a Reply