አፍሪካ ፡ የኮንፌድሬሽን ካፕ የምድብ ጨዋታዎች ዛሬ ይጀምራሉ

የ2016 ኦሬንጅ ካፍ ኮንፌድሬሽን ካፕ የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታዎች ዛሬ ማራካሽ ላይ በሚደረግ አንድ ጨዋታ ይጀምራል፡፡ ከ2007 በኃላ ለመጀመሪያ ግዜ የቱኒዚያ ሊግን ማሸነፍ የቻለው ኤቷል ደ ሳህል ከሜዳው ውጪ ሞሮኮ ላይ ከካውካብ ማራካሽን የሚያደርጉት ግጥሚያ የ2016 ኮንፌድሬሽን ካፕ መክፈቻ ጨዋታ ይሆናል፡፡

በታዋቂው ቱኒዚያዊው አሰልጣኝ ፋውዚ ቤንዛርቲ እየተመራ የሊጉን ክብር ከመዲናው ቱኒዝ ወደ ሶስ ያመጣው የዓምናው ኮንፌድሬሽን ካፕ አሸናፊ ኤቷል ደ ሳህል በኮንፌድሬሽን ካፑ ሳይጠበቅ ወደ ምድብ ከተቀላቀለው ካውካብ ማራካሽ ከባድ ፈተና ይገጥመዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በምድብ ሁለት የተደለደሉት ሁለቱ ክለቦች የአፍሪካ ክለቦች ውድድር ላይ ከፍተኛ ልዩነት ያላቸው ሲሆን በምድቡ ውስጥ ያሉት ሁሉም ክለቦች ከሰሜን አፍሪካ መሆናቸው ደግሞ ጨዋታዎቹ በእጅጉ አጓጊ አድርጓቸዋል፡፡ የሞሮኮ ቦቶላ ሊግን በታሪኩ ለመጀመሪያ ግዜ ያሸነው ፉስ ራባት በሜዳው አል አሃሊ ትሪፖሊን ዕሁድ ዕለት በምድቡ ሌላ ጨዋታ ያስተናግዳል፡፡ ፉስ ራባት የአምና ሻምፒዮኑን ዋይዳድ ካዛብላንካን በሁለት ነጥብ በመብለጥ የሊጉን ክብር ያሳካ ሲሆን አሃሊ ትሪፖሊን የማሸነፍ ቅድመ ግምቱንም ማግኘት ችሏል፡፡

ዕሁድ ሃያሉ የዲ.ሪ. ኮንጎው ክለብ ቲፒ ማዜምቤ ሉቡምባሺ ላይ በፋይናንስ ቀውስ ውስጥ የሚገኘውን የጋና ኤምቲኤን ኤፌ ካፕ የ2014/15 አሸናፊ ሚዲአማን ያስተናግዳል፡፡ ሚዲአማ ባለበት ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ምክንያት እራሱን ከውድድሩ ለማግለል እየፈለገ ነው፡፡ በፈረንሳዊው ሁበርት ቬሉድ የሚመራው ማዜምቤ ኮንፌድሬሽን ካፑን ማሸነፍ ዋነኛ እቅዱ ሲሆን አብዛኞቹ ዋሳኝ ተጫዋቾቹ በመልካም ጤንነት ላይ መገኘታቸው ለሚዲአማ ጨዋታው ያከብደዋል፡፡

በምድብ አንድ ሌላ ጨዋታ ብቸኛው የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ ያንግ አፍሪካንስ ከሜዳው ውጪ ኤምኦ ቤጃያን ይገጥማል፡፡ ያንጋ የታንዛኒያ ሊግን ያሸነፈ ሲሆን ለጨዋታው እንዲረዳው ዝግጅቱን በቱርክ አድርጎ ነበር፡፡ የውድድር ዓመቱን ከአልጄሪያ ሊግ ሻምፒዮን ዩኤስኤም አልጀር በ14 ነጥቦች ርቆ ስድተኛ ሆኖ የጨረሰው የቤጃያ ከተማው ክለብ በሴኔጋላዊው አጥቂ መሃመድ ዋሊዩ ንዶዬ እየተመራ የያንጋን የተከላካይ ክፍል ይፈትናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 

አርብ ሰኔ 10/ 2008

22፡30 – ካውካብ አትሌቲክ ክለብ ማራካሽ (ሞሮኮ) ከ ኤቷል ስፖርቲቭ ደ ሳህል (ቱኒዚያ) (ግራንድ ስታደ ማራካሽ)

 

ዕሁድ ሰኔ 12/2008

15፡30 – ቲፒ ማዜምቤ (ዲ.ሪ. ኮንጎ) ከ ሚዲአማ (ጋና) (ስታደ ቲፒ ማዜምቤ)

22፡00 – ፋት ዩኒየን ስፖርት ራባት (ሞሮኮ) ከ አል አሃሊ ትሪፖሊ (ሊቢያ) (ኮምፕሌክ ስፖርቲፍ ሞላይ አል ሃሰን)

22፡15 – ሞሊዲያ ኦሎምፒክ ቤጃያ (አልጄሪያ) ከ ያንግ አፍሪካንስ (ታንዛኒያ) (ዩናይት መግሪቢን)

Leave a Reply