ታክቲካዊ ትንታኔ ፡ መከላከያ 0-1 ሲዳማ ቡና

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 10ኛ ሳምንት የመጀመርያ ጨዋታ በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ የነበሩት ሲዳማ ቡና እና መከላከያ ተፋልመው የዘላለም ሽፈራው ሲዳማ ቡና ባለሜዳውን በማሸነፍ የጉን መሪነት አስከብሯል፡፡ የሶከር ኢትዮጵያው ሚልኪያስ አበራ ጨዋታውን ተመልክቶ የሚከተለውን ታክቲካዊ ትንታኔ አዘጋጅቷል፡፡

የአዲስ አበባ ስታድየም እድሳት ላይ በመሆኑ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአዲስ አበባ ጨዋታዎች እየተካሄዱ የሚገኙት በአበበ ቢቂላ ስታድየም ነው፡፡ በዚህ በ10ኛው ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር የገብረመድን ኃይሌ መከላከየ በዘላለም ሽፈራው የሚመራው ሲዳማ ቡናን በሜዳው አስተናግዷል፡፡

በጨዋታው ሲዳማ ቡናዎች 4-4-2 (በጨዋታ ሒደት ወደ 4-4-1-1 የሚቀየር) የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደር የተጠቀሙ ሲሆን መከላከያዎች ደግሞ ከወትሮው በተለየ መልኩ 4-3-3 የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደርን (ፎርሜሽን) በጨዋታው የመጀመርያ አጋማሽ ለመተግበር ሞክረዋል፡፡

(ምስል 1)

 

የመጀመርያዎቹ 15 ደቂቃዎች

መከላከያ በዘንድሮው የውድድር ዘመን በመስመር አማካኝነት ሚና የሚጠቀምባቸው ተጫዋቾች በአብዛኛው በመሃለኛው የሜዳ ክልል ላይ መሰለፍን የሚመርጡ ከመሆናቸው አንፃር 4-4-2ን አጨዋወት ሲስተሙን ወደ 4-3-3 መቀየሩ አግባብ ይመስላል፡፡

ከዚህ ቀደም እንደታየው ቡድኑ በሁለቱ የመስመር ተከላካዮቹ (ዮሃንስ እና ሽመልስ) ከሚያገኘው የሰፋት (Width) ጥቅም ውጪ በመስመር ላይ በሚያሰልፋቸው አማካኞች ሜዳን ወደ ጎን ለጥጦ የመጨወት ስርአት (Width) ሲተገበር አልተስተዋለም፡፡ ይህም ለቡድኑ አጥቂዎች (መሃመድ እና ሙሉአለም) ከመስመር የሚላኩ ተሸጋሪ ኳሶች እንዳይደርስ አድርጎታል፡፡ በተጨማሪም ፉልባኮቹ በመስመሩ ጥግ ሰፊ ርቀትን እንዲሸፈፍኑ ሲየያስገድዳቸው ታይቷል፡፡ በተለይ (Overlap) ለማድረግ ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክፍል ሲገቡ ከኋላቸው የሚተዉት ክፍተት ለተደጋጋሚ ጥቃት ሲያጋልጣቸው ይታያል፡፡

በዚህኛው ጨዋታ በግራ መስመር የተሰለፈው ፉልባክ (ቁጥር 3) ሚዛናዊ ያልሆነው በማጥቃት ላይ ብቻ ያተኮረው የፊት ለፊት ሩጫ በሌላ የመስመሩ ተጫዋቾች ባለመታገዙ ምክንያት ትቶት የሚሄደው ክፈተትን ሲዳማዎች በኬንያዊው አጥቂያቸው ኤሪክ ሙራንዳ (13) ፤ በእንዳለ ከበደ (7) እና በቢንያም አድማሱ (3) አማካኝነት በተደጋጋሚ ሊጠቀሙበት ሞክረዋል፡፡

የመከላከያ የመስመር አማካኞች ወደ መሃለኛው ክፍል ላይ ባዘነበለው እንቅስቃሴያቸው በተጋጣሚ ለይ የመሃል ሜዳ የቁጥር የበላይነት ሊያስገኝላቸው ቢችልም የተጋጣሚውን ፉልባኮች እዛው አፍነው በመያዝ (stifle በማድረግ) የሚወጡትን የመከላከል ኃላፊነት እንዳይተገብሩ ሲያደርጋቸው ይታያል፡፡ በዚህም ምክንያጽ 4-3-3ን መጠቀም የተሻለ አማራጭ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡

ሆኖም በመጀመርያዎቹ 15 ደቂቃዎች በመከላከያዎች የግራ መስመር ተከላካይ (ቁጥር 3) የተፈጠረውን ክፍተት በመጠቀም ሲዳማዎች በተጋጣሚ የሳጥን ክልል የሚገኙትን ሁለቱን አጥቂዎቻቸውን (አንዱአለም እና ኤሪክ) ያማከሉ ረጃጅም ኳሶችን ሲጥሉ ነበር፡፡ በዚህ ሂደት በተገኘው ቅጣት ምትም ሶስት ነጥቦች ይዘው እንዲወጡ ያደረጋቸውን ግብ ፍፁም ተፈሪ (5) በ18ኛው ደቂቃ ግብ እዲያስቆጥር ረድቶታል፡፡

ምስል 2

 

Image 2
Image 2

የአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው የመጀመርያው የተጫዋች ለውጥ እና ተፅእኖ

የሲዳማ ቡናው አሰልጣኝ በ13ኛው ደቂቃ የቀኝ መስመር ተከላካካቸው ዘነበ ከበደ (2) ተጎድቶ ሲወጣ ያስገቡት ተጫዋች (ቁጥር 8) ከዘነበ በበለጠ ወደፊት በመጠጋት የመከላከያን የግራ መስመር ፉልባክና በመስመሩ ተጠግቶ ሲጫወት የነበረው ሚካኤል ደስታን (13) የማጥቃት እንቅስቃሴ እንዲቀንስ ለማድረግ ችሏል፡፡ የሲዳማ የመሃል አማካዮች (ቢንያም እና ፍፁም) በተደጋጋሚ የፊት ለፊት ሩጫ ሲያደርጉ ተtከላካይ ክፍሉ አበሯቸው ወደፊት መንቀሳቀሱ በተከላካይ እና በአማካይ መስመር መካከል የሚኖረውን ክፍተት (Between the lines) እንዲጠብ አድርጎታል፡፡ ይህም ቡድኑ በማጥቃትም ይሁን በመከላከል እንቅስቃሴ ተጠቅጥቀው (ኮምፓክት ሆነው) መቅረባቸውን አመልካች ነው፡፡ በተጨማሪም አንዱአለም ንጉሴ (21) ወደኋላ እየተመለሰ የመከላከያን የመሃል ሜዳ የቁጥር ብልጫ ለማካካስ የሚደረገው እቅስቃሴ ቡድኑን የበለጠ ጠንካራ (solid) አድርጎት አምሽቷል፡፡ በመሃል ተከላካይ መስመር የተሰለፈው ሞገስ ታደሰ (28) እና በቀኝ መስመር ፉልባኩ (ቁጥር 8) መካከል የነበረው መገግባባት እና የመተጋገዝ ሒደት ከቡድኑ ጠንካራ ጎኖች አንዱ ነበር፡፡

ምስል 3

Mekelakeya 0-1 Sidama (3)

የአሰልጣኝ ገብረመድህን ታክቲካዊ ለውጥ

የመከላከያው አሰልጣኝ በ39ኛው ደቂቃ በተጫዋችም በአጨዋወትም ለውጥ አደረጉ፡፡ በግራ መስመር የመስመር አጥቂነት (Wide forward) ሚናን ሲወጣ የነበረው ቁጥር 26ን አስወጥተው በዛው መስመር በመስመር አማካኝነት የሚሰለፈው ሳሙኤል ታዬን (19) አስገቡ፡፡ በዚህ ሒደትም የመከላከያ የአጨዋወት ቅርፅ ወደ 4-4-2 ተቀየረ፡፡ ወደ ቀኝ የማጥቃት ክልል አዘንብለው ሲጫወቱ የነበሩት መሃመድ እና ሙሉአለም በመካከላቸው የነበረውን ርቀት በማስፋት የበለጠ (Space) መጠቀም ጀመሩ፡፡ ቀስ በቀስ የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን እንዲሁም ሚዛናዊ የሆነ የማጥቃት / የመከላከል እንቅስቃሴን መተግበር ቻሉ፡፡ በሳሙኤል አማካኝነት መጠነኛ የስፋት (Width) ጥቅም ማግኘትም ጀመሩ፡፡ ሳሙኤል (multi – directional) ተጫዋች ከመሆኑ አንፃር በግራው መስመር ፉልባኩ (ቁጥር 3) እና ሚካኤል ደስታ ጋር በመሆን የሲዳማ ቡናዎች የቀኝ መስመር ተጫዋቾች ላይ የቁጥር ብልጫ (overload) ማድረግ ችለዋል፡፡ ይህም የሲዳማ ቡናዎችን የመሃል አማካዮች ይበልጥ ወደኋላ እንዲሳቡና በመከላከሉ ላይ እንዲያተኩሩ በማድረጉ አማካዩ እና አጥቂው መካከል ያለው ክፍተት እንዲሰፋ አድርገዋል፡፡ በዚህም ምክንያት አንዱአለም ንጉሴ ወደኋላ እየተሳበ አጥቂው እና አማካኞቹን እንዲያገናኝ (link እንዲያደርግ) አስገድዶታል፡፡

ምስል 4

 

ምስል 4
ምስል 4

ሁለተኛው አጋማሽ

በሁለተኛው አጋማሽ ሲዳማዎች በአብዛኛው በመከላከል ላይ ያተኮረ አጨዋወትን ሲተገብሩ አምሽተዋል፡፡ ሁለት እጅግ የተቀራረበ ባለ 4 ተጫዋች መስመር (deep banks of four) በመስራት በመስመሮቻቸው መካከል ያለውን ክፍተት በማጥበብ የመከላከያ ተጫዋቾችን የመቀባበያ አማራጮች (በተጋጣሚ ሜዳ ያለቸውን) እንዲሁም የማጥቃት እንቅስቃሴን የሚያሰፋ ማእዘናትን (Attacking Angles) ሲከላከሉ ነበር፡፡

ባለሜዳው ቡድን በቀኝ ፉልባኩ ሽመልስ አማካኝነት በተደጋጋሚ የፊት ለፊት ሩጫ ማጥቃት ላይ ያተኮረ (ኦቨርላፒንግ ሙቭመንት) ከፊት ለፊቱ ያሉት አማካዮች ወደግራው መስመር አዘንብለው በመጫወታቸውና ሽመልስ አጋዥ በማጣቱ ሲመክኑ ተስተውሏል፡፡

በመከላከያ የግራው መስመር ተክለወልድ ፍቃዱ (8) በሃይሉ ግርማ (21) እና ሚካኤል ደስታ (13) የሲዳማ ቡና ወደቸ ኋላ ማፈግፈግን በመመርኮዝ (overload) አድርገው የተጠቀጠቀውን የተከላካይ መስመር ለማስከፈትና በዛው መስመር ወደኋላ እየተመለሰ ሲጫወት የነበረውን ሙሉአለምን ለማገዝ የነበራቸው እቅድ የቀኝ መስመራቸውን እንዳይጠቀሙበት ያደረጋቸው ይመስለኛል፡፡በዚህኛውም አጋማሽ ሳሙኤል የግራ እግር ተጫዋች በመሆኑ ይበልጥ ወደ መሃል እየገባ ተጫውቷል፡፡

አሰልጣኝ ዘላለም የመጨረሻ ደቂቃ ቅያሪዎች የመከላከል አጨዋወቱን የበለጠ የሚያጠናክሩ ጥንቃቄ የታከለባቸው የተጫዋቾች ለውጥ ቡድኑ ውጤቱን አስጠብቆ እነዲወጣ አስችሏል፡፡ ጨዋታውም በእንግዳው ቡድን 1-0 አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡

ምስል 5

Mekelakeya 0-1 Sidama (5)

ያጋሩ